ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሀብታሙ ሽዋለም ብቸኛ ግብ ድል ሲቀናው ባህርዳር ከተማ እና ነገሌ አርሲ ነጥብ ተጋርተዋል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሀብታሙ ሽዋለም ብቸኛ ግብ ድል ሲቀናው ባህርዳር ከተማ እና ነገሌ አርሲ ነጥብ ተጋርተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4 ኛው ሳምንት የምድብ ሁለት የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናው የጣና ሞገዶቹ እና ሰጎኖቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀኑ 7:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ጅማሮን ያደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ቡናማዎቹ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የግራ መስመር አማኑኤል አድማሱ ያሻገረውን ኳስ ሙሀመድ ሻቫን ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው አሸብር እንደምንም ብሎ ማዳን ችሏል። ጨዋታውም ሌሎች ሙከራዎችን ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ 48ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሜዳው የግራ ክፍል ያገኙትን ቅጣት ምት ሀብታሙ ሽዋለም በቀጥታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ቡናማዎቹ 59ኛው ደቂቃ ላይ ሙሀመድ ሻቫን በግንባሩ ሞክሮ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት ኳስ አስቆጪ ነበር። በኤሌክትሪክ በኩል እዮብ ገ/ማርያም 70ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋት እንዲሁም በቡናማዎቹ በኩል
75ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ አርሲ ነገሌ


በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀኑ 10:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ባህር ዳር ከተማን ከ አዲስ አዳጊው አርሲ ነገሌ አገናኝቷል። በጨዋታው ጅማሮ የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ ከአርሲ ነገሌው ዲሰሬ ፓስካል ጋር በጨዋታ መሀል ተጋጭተው ግብጠባቂው ፔፔ ከበድ ያለ ጉዳት በማስተናገዱ ለተሻለ ህክምና ለማግኘት አምርቷል። በአጋማሹ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ አማካይ ሄኖክ ይበልጣል የሞከረው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። በድጋሚ 41ኛው ደቂቃ ላይ ኩዋሜና ቧቲንግ በመስመር ይዞት የገባውን ያለቀለት የግብ ዕድል ግብጠባቂው አምክኖበታል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር አስመልክተውናል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሰች ግብን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ በተቃራኒው አርሲ ነገሌዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሜዳቸው ላይ በቁጥር በዛ ብለው መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል። በአጋማሹ በሁለቱም ቡድን በኩል ይሄ ነው የሚባል የጌብ ሙከራዎችን ሳያስመለክቱን ጨዋታው ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።