ከዕረፍት በፊት አራት ጎል በተቆጠረበት ጨዋታ ፈረሰኞቹ ጣፋጭ ድል ሲቀዳጁ ኢትዮጵያ መድን እና አዞዎቹ ያለ ግብ ተለያይተዋል::
ባህር ዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

7:00 ሲል የተጀመረው የምድብ አንድ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቷል። በግብ በተንበሸበሸው ጨዋታ ገና ከጅማሮው አንስቶ በግብ የታጀበ ሲሆን 3ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳሩ ግብ ጠባቂ ይገርማል መኳንንት ለማቀበል ሲሞክር የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው ተገኑ ተሾመ አመቻችቶ ለአቤል ያለው ያቀበለው ሲሆን አቤልም ወደ ግብነት በመቀየር ፈረሰኞችን መሪ ማድረግ ችሏል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል፤ ከሜዳው የቀኝ ክፍል ሄኖክ ዮሐንስ ያቀበለውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አቤል ያለው ኳስን ከመረብ ጋር በማገናኘት ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ 34ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ጥጋቡ ከሳጥን ውጭ ጥሩ የሆነ ግብን በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል። ፈረሰኞቹ የተቆጠረባቸውን ግብ ለማረም ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰዓት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ከግራ መስመር የተቀበለውን ኳስ አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጭ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን በሁለት ግብ ከፍ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት የጣና ሞገዶች ቀይረው ባስገቡት አማኑኤል ገ/ ሚካኤል አማካኝነት ሶስት ለግብ የቀረቡ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግን የፈረሰኞችን የመከላከል አጥር ንደው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በፈረሰኞቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ አርባ ምንጭ ከተማ

10:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን ከ አርባ ምንጭ ከተማ አገናኝቷል:: ጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን በሙከራ ረገድ ተቀዛቅዞ ደካማ የሆነ የመጀመሪያ አጋማሽን ተመልክተናል። 17 ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ ያሻገውን ኳስ አለን ካይዋ አግኝቶ ወደ ግብ የሞከረው ቢሆንም በግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ አማካኝነት ግብ ከመሆን ድኗል። ከዚህ ሙከራ በስተቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ የቀጠለው ሁለተኛ አጋማሽ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ይሁን እንዳሻው 51ኛ ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። መድኖች ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ያሬድ ካሳየ በግንባሩ ገጭቶት የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ኳስ ውጪ ሌላ ያለቀለት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ አዞዎቹ በአንጻሩ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የወሰዱትን ኳስ ኤፍሬም ታምራት በትክክል ወደ ውስጥ መቀነስ ሳይችል በመቅረቱ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታውም ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

