“ቀጣይም የምናስተናግዳቸው ውድድሮች ይኖራሉ”

“ቀጣይም የምናስተናግዳቸው ውድድሮች ይኖራሉ”


👉 “የተሻለ ውጤት ከመጣም በመንግስት ደረጃ  የተሻለ ድጋፍ የሚጠብቃቸው …..”

👉 “ሀገራችን ለአራተኛ ጊዜ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ የምታልፍበት ዕድል ስለሆነ በጥብቅ ‘ዲሲፕሊን’ በመንግስት ደረጃም በእግር ኳስ ፌዴሬሽንም….”

በኢፌድሬ ባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስተር ድኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ ለሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር  የተደረገው ቅድመ ዝግጅት አስመልክተው የሰጡት ሀሳብ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር እንደምታስተናግድ ይታወቃል። ዛሬም ለውድድሩ የተደረገው ቅድመ ዝግጅት እንዲሁም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ በኤልያና ግራንድ ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል። በመግለጫውም በኢፌድሬ ባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስተር ድኤታ አቶ መኪ መሐመድ የሰጡትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

“ይህ ውድድር ሀገራችን እንድታስተናግድ ከእግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር የተነጋርንበት ሁኔታ ነበር፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖም ሀገራችን ውድድሩን እንድታስተናግድ ተመርጣለች። እንደ አጠቃላይ ለዚህ የሚያስፈልጉ ከሀገር አቀፍ ጀምሮ እስከ ውድድር ስፍራ ድረስ ኮሚቴ ተደራጅቶ ሁሉም ወደ ስራ የገባበት ሁኔታ ነው ያለው፤ አሁን ወደ መጠናቀቁ ደርሷል። ውድድሩ ከስር በላይ ሀገራት  የሚሳተፉበት ነው በአጠቃላይ ከ350 እስከ 400 ልዑካን ቡድን ወደ ሀገራችን ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን። ይሄን ውድድር ስናዘጋጅ መንግስት አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ለሁሉም ሴክተሮች መመርያም ጭምር የተሰጠበትና ስፖርቱም ያሉትን ዕድሎች
በማስተናገድ ከስፖርቱም ባለፈ በአጠቃላይ ለሀገራችን ቱሪዝምና ሀገር ገፅታ ያለው ጥቅም የጎላ በመሆኑ በርካታ ውድድሮች እንድታስተናግድ እየሰራን እንገኛለን፤ ቀጣይም የምናስተናግዳቸው ውድድሮች ይኖራሉ።

ውድድሩ በሁለት ቦታ የሚካሄድ ይሆናል ዝግጅቱ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል። ለዚህ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተደራጅተዋል፤ የፀጥታ ኮሚቴ አጠቃላይ ውድድሩ ጤናማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ካለ ምንም እንከን እንዲካሄድ ሙሉ ዝግጅት የተጠናቀቀበት ሁኔታ ስላለ በተሻለ መንገድ ይደረጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይሄንን ደግሞ የሚድያ አካላት ሽፋን እየሰጡ አጠቃላይ የሀገራችን ስፖርት እንዲነቃቃ ያለው ሚና ትልቅ በመሆኑ በተለይም ደግሞ እግር ኳሳችን ካለበት ሁኔታ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ ውድድሩን በጋራ በተሻለ መንገድ እየገለፅን እንሄዳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ከከዚህ ቀደም በተሻለ መንገድ ታዳጊ ላይ የተሰራበት ሁኔታ ነው  ያለው። ለዚህ ደግሞ ‘Road to’ 29 በሚል ፕሮጀክት በጥሩ ሁኔታ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረበት ሁኔታና ወጣቶች በዚህ ላይ ዝግጅት እንዲያደርጉበት ከዚህ ባለፈም በዚህ ውድድር ራሳቸውን የሚፈትሹበት፤ ሀገራችን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ የምታልፍበት ዕድል ስለሆነ በጥብቅ ‘ዲሲፕሊን’ በመንግስት ደረጃም በእግር ኳስ ፌደሬሽንም በመቀናጀት እንዲሁም ይሄንን ቡድን ስያዘጋጁ ከነበሩ አጠቃላይ አካላት ጋር ስንነጋገርበት የነበረ ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚ የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህም ባለፈ ወጣቶቹ ቀጣይ ለምናደርጋቸው የአዋቂዎች ውድድር የሚያድጉበት ስለሆነ የተሻለ ይሆናል፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ብለን የምንቀርብበት፣ የክትትል ሁኔታውን ትንሽ ጠበቅ የምናደርግበት ነው። እንዲሁም የተሻለ ውጤት ከመጣም በመንግስት ደረጃ  የተሻለ ድጋፍ የሚጠብቃቸው መሆኑ በዚሁ አጋጥሚ እገልፃለሁ”።