“ሀገሪቱ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው እግርኳስ ይገባታል።”
አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር
“ለእያንዳንዱ ‘ታለንት’ የመጫወት ዕድል መስጠት አለብን ብለን እናምናለን።”
አሰልጣኝ አምሳሉ ጥላሁን
ቀደም ብለን ሀገራችን በምታስተናግደው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር ዙርያ የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስተር ድኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ የሰጡትን ሀሳብ ማቅረባች ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች አምሳሉ ጥላሁን እና ቤንጃሚን ዚመር ከሰጡት ሃሳብ አንኳር ነጥቡን አቅርበንላችኋል
አሰልጣኝ አምሳሉ ጥላሁን
“ለእያንዳንዱ ‘ታለንት’ የመጫወት ዕድል መስጠት አለብን ብለን እናምናለን፤ ከተጫወቱ በኋላ እንምረጥ ከዛ ያንን ‘ታለንት’ አሳድገን በትልቅ ደረጃ እንወዳደር ብለን ነው ፕሮጀክቱን ያቀረብነው። የፈለገ እኛ ብንዘጋጅ ተጋጣሚም ተዘጋጅቶ ነው የሚመጣው የሚሆነው እናያለን። አንድ ችግራችን የነበረው ‘ቪድዮ’ እንደፈለግክ አታገኝም ግን ተጋጣሚያችን በተቻለ መጠን ለማየት ሞክረናል። ስለ ተጋጣሚያቸው እንዲሁም ስለ ራሳችን እየተዘጋጀን ነው”።

አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር
“በመጀመርያ ደረጃ ድጋፍ ላደረጉልን የስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ማመስገን እፈልጋለው። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ራዕይ አላቸው። ኢትዮጵያ እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ ያላት ሀገር ናት። ስለዚህ ሀገሪቱ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው እግርኳስ ይገባታል። በምስራቅ አፍሪካ መነቃቃት እንዳለ ግልፅ ነው፤ ሌሎች ሀገሮች በመሻሻል ላይ ናቸው፤ ጥቂት እርምጃዎችም ቀድመዋል። ስመጣ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው የቤቴ ያክል ስሜት የተስማኝ፤ ድንቅ ባህል ያላችሁ ድንቅ ህዝቦች ናችሁ፤ ሙዚቃው፣ ምግቡ፣ እንግዳ ተቀባይነቱ እንዲሁም ኳሱ። በዓለም ዙሪያ ተጉዣለሁ ኢትዮጵያ ለየት ያለ ስሜት ያላት ሀገር ነች”።
“ለቡድናችን አባላትን ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በጣም ጠንክረን ሰርተናል፤ አንዳንድ ጊዜ ከጠዋት እስከ እኩለ ለሊት ድረስ እንሰራ ነበር። እዚህ መዳበር የሚችል ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች አሉ። የእኛ ሀሳብ ደግሞ እነዚህን ወጣቶች በዘመናዊ የእግር ኳስ መንገድ ለማሳደግ መሞከር ነው። እውን እየሆነ ነው ብዬም አስባለሁ። የመጀመርያ ግባችን በጥሩ መንገድ መጫወት ነው፤ በጥሩ ሁኔታ ከተጫወትንም ጥሩ ውጤት እናገኛለን። ከፍተኛ ድጋፍ አለን እና ደጋፊዎች እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች ህልማቸውን እንዲያሳኩ መደገፍ አለባቸው”።


