ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ መሪ በነጥብ ለመስተካከል የዛሬው ጨምሮ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት የሚፋለሙቡት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
በአራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበው 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ግዮርጊሶች ከግሩም ብቃት ጋር ባህርዳር ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፉበት የሊግ ጨዋታ በኋላ በኢትዮጵያ ዋንጫ በአርባምንጭ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ከመሪው ጋር በነጥብ ለመስተካከል ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ።

ካከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገዱት እንዲሁም ለጥቃት እምብዛም የማይጋለጥ የኋላ ክፍል ያላቸው ፈረሰኞቹ በመከላከሉ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ በአወንታ የሚጠቀስ ቢሆንም የፊት መስመራቸው ግን የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። በእርግጥ ቡድኑ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ከነገሌ አርሲ ጋር ጉልህ የአፈፃፀም ድክመት ፤ ከሸገር ከተማ ጋር ደግሞ ንፁህ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ድክመት ተስተውሎበታል። በማጥቃት አጨዋወቱ የሚስተዋለው የወጥነት ችግር መቅረፍም የቡድኑ ቀዳሚ የቤት ስራ ነው።
ባከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው አምስት ነጥቦች በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከሁለቱ ቀሪ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከመሪዎቹ እንዲደላደሉ ዕድል ስለሚሰጣቸው ወደ ዛሬው ጨዋታ በልዩ ትኩረት እንደሚቀርቡ እሙን ነው። ባለፈው ዓመት በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ከነበራቸው ክለቦች በቅድምያ የሚጠቀሰው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ መረቡን አስከብሮ በመውጣት ጥንካሬውን ማስቀጠል ቢችልም በማጥቃቱ ረገድ ግን የቀድሞ ጥንካሬው ላይ አይገኝም። የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ደረጃ ከፍ ማድረግም የኢትዮጵያ መድኖች ዋነኛው ስራ ይሆናል።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 29 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 19 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 50 ጎሎች ፣ 3 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረው 7 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

