ሲዳማ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ ያደረጉት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ6ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የመጀመርያ ቀን ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልታየበት እንዲሁም በሙከራዎች ያልታጀበ ነበር።

በአንፃራዊነት የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ በነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች በኩል መስፍን ታፈሰ ከመስመር አሻግሯት
ብለስ ናጎ አክርሮ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ ባዳናት እንዲሁም ብርሃኑ በቀለ ከቆመ ኳስ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ መቐለ 70 እንደርታዎችም በአብርሀም ጌታቸው የርቀት ኳስ አማካኝነት እንዲሁም ተመስገን ተስፋዬ ከመዓዝን የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ባደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

በፉክክር ረገድ የተሻለ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ በሚባል እንቅስቃሴ ቢጀምርም የኋላ የኋላ የሲዳማ ቡናዎች ብልጫ የታየበት ነበር። ሲዳማ ቡናዎች ወደ ፊት በመሄድ ረገድ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ቢችሉም ዮሴፍ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር አክርሮ በመምታት ካደረጋት፤ ተመስገን በጅሮንድ አክርሮ መቷት ዘርኢሰናይ ብርሃነ በግንባር ከመለሳት እንዲሁም ብለስ ናጎ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ሶፎንያስ ሰይፈ ከተመለሰችው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በ74′ ደቂቃ ተከላካዩ ዘርኢሰናይ ብርሃነን በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ ወደ ሳጥናቸው አፈግፍገው ለመከላከል የመረጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ስድስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች እንዲሁም 30 ጥፋቶች የተፈፀሙበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


