ሪፖርት| ሀዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሀዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት የምድብ አንድ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማዎች በብሩክ ታደለ ብቸኛ ግብ ወልዋሎን ሲያሸንፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሀዋሳ ከተማ


በመጀመርያው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ ቢሆኑም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ በአንፃራዊነት ወልዋሎዎች ብልጫ ነበራቸው። ብሩክ እንዳለ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ የተመለሰው ኳስ እንዲሁም አማካዩ በሜዳው የቀኝ ክፍል ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት በግቡን አግዳሚ ታኮ ለጥቂት የወጣው ሙከራ ባቢጫ ለባሾቹ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። በአጋማሹም ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተጫዋች ቅያሪ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ሀዋሳ ከተማዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ ብሩክ ታደለ ከቢንያም በላይ የተላከችለትን ኳስ ተከላካይ ቀንሶ በመግባት በጠባብ ‘አንግል’ ያስቆጠራት ግብም ሀይቆቹን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ቢንያም በላይ ከያሬድ ብሩክ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር መገናኘት ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ውጤቱንም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በብሩክ ታደለ ብቸኛ ግብ ወልዋሎ ዓ/ዩን ማሸነፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወላይታ ድቻ

የምድብ አንድ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታው ገና በጅማሮው ግብ ያስመለከተን ነበር። ዋና ዳኛ መለሰ ንጉሴ ጨዋታው መጀመሩን በፊሽካቸው ካበሰሩ ከ4 ደቂቃ በኋላ ካርሎስ ዳምጠው ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ሁለት ተከላካዮችን አሳልፎ የሰጠውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ ወደ ግብነት ቀይሮ የጦና ንቦችን መሪ አድርጓል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ 16 ደቂቃዎች ሲቀሩትም የወላይታ ድቻ ተጫዋች ከመስመር የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማውጣት ሲሞክር በስህተት ወደ ራሱ ግብ መቷት የግብ አግዳሚ ገጭታ ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ ለንግድ ባንኮች እጅግ አስቆጪ ዕድል ነበረች።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በብዙ ነገር ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ሙከራ ሳያስመለክቱን የቆዩ ቢሆንም 83ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቅያሪያቸው ትክክል መሆኑን ያስመሰከሩበትን ግብ ንግድ ባንኮች አስቆጥረዋል። ተቀይረው በገቡት ኤፍሬም ሌጋሞ እና ናትናኤል ዳንኤል በፈጠሩት ጥምረት ከኤፍሬም ሌጋሞ የተቀበለውን ኳስ ናትናኤል ዳንኤል ወደ ግብነት ቀይሮ የማታ ማታ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ይህንን ተከትሎም ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።