ሪፖርት| መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሁለት ቀይ ካርዶችን ባስመለከተን ጨዋታ ጦሩ እና ብርቱካናማ ለባሾቹ 1-1 ተለያይተዋል።

የስምንተኛ ሳምንት የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታ መቻልን ከ ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘ ሲሆን 30ኛው ደቂቃ ላይ የመቻሉ መናፍ አሞሮ የድሬዳዋው አቡበከር ሻሚል ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በጨዋታው ዋና ዳኛ ሀይሚኖት አዳነ ውሳኔ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። የቁጥር ብልጫውን እንደ መልካም አጋጣሚ የወሰዱት ድሬዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሻሚል ከአማካይ ክፍል በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ረጅም ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የቆየው መሐመድኑር ናስር ወደ ግብነት ቀይሮ ብርቱካናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

መቻሎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደጋግመው መድረስ የቻሉ ሲሆን 45+3 ላይ ከሜዳው የግራ ክፍል አብዱልከሪም ወርቁ ያሻማውን ኳስ ቻርለስ ሙሰጌ አግኝቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብጠባቂው አብዩ ኪሳዬ በጥሩ ብቃት መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ለመናፍ የቀይ ካርድ መገኘት ምክንያት የነበረው የድሬዳዋው አቡበከር ሻሚል 51ኛው ደቂቃ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተለይ ከቀይ ካርዱ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የጨዋታውን ብልጫ የወሰዱት መቻሎች 57ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሽድ ለማራቅ ሲሞክር ተጨርፎበት ያገኘውን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ ወደ ግብ ቢሞክርም የግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን ታድጎበታል።

በቁጥር እኩል መሆን የቻሉት መቻሎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊን ኮፊ በጥሩ ቅልጥፍና የድሬዳዋ ተከላካዮችን በማለፍ ያቀበለውን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ መቻሎች ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።