ሪፖርት|  ፈረሰኞቹ ወደ ድል ሲመለሱ ሳቢ የነበረው የአዲስ አዳጊዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ወደ ድል ሲመለሱ ሳቢ የነበረው የአዲስ አዳጊዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ8ኛው ሳምንት ምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ድል ሲመለሱ አራት ግቦች የተቆጠሩበት የነገሌ አርሲ እና ሸገር ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍፃሜ አግኝቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ


በሁሉም ረገድ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ ቡድኖቹ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ወደ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ጥቂት ነበሩ። በአዞዎቹ በኩል መሪሁን መስቀለ አሻግሮት ታምራት እያሱ በግንባር ያደረገው እንዲሁም ሳሙኤል አስፈሪ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አሻምቶት ታምራት እያሱ በግምባር ያደረጋት ሙከራ ሲጠቐሱ በፈረሰኞቹ በኩል ሀብታሙ ጉልላት አክርሮ ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች። በ43 ደቂቃ ግን ፈረሰኞቹ ጨዋታውን መምራት ችለዋል፤ ተገኑ ተሾሙ ከግራ መስመር አሻግሯት ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ በአግባቡ ያልተቆጠራት ኳስ ተጠቅሞ ፀጋ ከድር ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም መለክያዎች የተሻለ፣ ማራኪ ፉክክር የተደረበት እና በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረበት ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል አፈወርቅ ኃይሉ ከመስመር አሻግሯት ቢንያም ፍቅሬ ያደረጋት፤ ተገኑ ተሾመ ከአማካዩ አፈወርቅ ኃይሉ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራ እንዲሁም ተከላካዩ ሄኖክ ዮሐንስ ያደረጋት ሙከራ ተጠቃሽ ሲሆኑ በአዞዎቹ በኩልም ኤፍሬም ታምራት አሻምቷት ታምራት እያሱ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ባዳናት ኳስ እንዲሁም እንዳልካቸው መስፍን ወደ ሳጥን አሻግሯት ታምራት እያሱ አብርዶ መቷት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ባወጣት ሙከራዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

በጨዋታው መገባደኛ ቢንያም ፍቅሬ በመልሶ ማጥቃት ያገኛትን ኳስ ገፍቶ ከግቡ አፋፍ ነፃ ለነበረው ተገኑ ተሾመ አቀብሎት የፊት መስመር ተጫዋቹ ያመከነው እጅግ የማይታመን ዕድልም በጨዋታው ከታዩ ለየት ያሉ ክስተቶች አንዱ ነው። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታውም በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ነገሌ አርሲ ከ ሸገር ከተማ


የመጀመርያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እንዲሁም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የነገሌ አርሲ ብልጫ የታየበት ነበር። ከቤ ብዙነህ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ አክርሮ መቷት ባህሩ ነጋሽ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ እንዲሁም ዘሩባቤል ፈለቀ ከመዓዝን ተሻግራ የሸገር ከተማ ተጫዋቾች የመለሷትን ኳስ አግኝቶ ለዳዊት ተፈራ ካቀበለው በኋላ አማካዩ መቷት በግቡ አፋፍ የነበረው ገብረመስቀል ዱባለ ጨርፏት ባህሩ ነጋሽ የመለሳት ኳስም ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። ከቤ ብዙነህ ከዳግማዊ አርዓያ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም ተጠቃሽ ናት። በ36ኛው ደቂቃ ላይ ካሌብ በየነ አሻግሯት በሳጥኑ የግራ ክፍል የነበረው አንተነህ ተፈራ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስም በሸገር ከተማ በኩል የተደረገች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነች።

ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ በአስደናቂ ፉክክር የታጀበ ማራኪ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነበር። በ55ኛው ደቂቃም ተሻሽለው የቀረቡት ሸገር ከተማዎች ናትናኤል ዘለቀ በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን አሻግሯት ጀቤሳ ምኤሳ ከመረብ ጋር ባዋሀዳት ኳስ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ በኋላ ዕድሎች ቢፈጠሩም የጠሩ ሙከራዎች ሳይደረጉ ከቆዩ በኋላ በ70ኛው ደቂቃ አሚር አብዱ እና ጀቤሳ ምኤሳ በሳጥኑ ግራ ክፍል አንድ ሁለት ከተቀባበሉ በኋላ ጀቤሳ ምኤሳ በጥሩ መንገድ ወደ ግብነት በቀየራት ኳስ ሸገር ከተማዎች መሪነታቸው አጠናክረዋል።

በአጋማሹ ተቀዛቅዘው ከቆዩ በኋላ ዳዊት ተፈራ ቆመ ኳስ ባደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ነገሌ አርሲዎች በ75ኛው ደቂቃ ከቤ ብዙነህ ከምስጋናው መላኩ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ባስቆጠራት እጅግ ማራኪ ግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል። ከግቧ በኋላ የተነቃቁት እና አለኝታ ማርቆስ ከቆመ ኳስ ባደረጋት ሙከራ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ነገሌ አርሲዎች በ90+2 ሮሆቦት ሶላሎ ከርቀት ባስቆጠራት አስደናቂ የቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ አራት ግቦች ያስመለከተው ማራኪ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።