ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች |  የዘጠነኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች |  የዘጠነኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እየተመሩ እስካሁን ባደረጓቸው ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ብቻ በማሸነፍ በአምስቱ ነጥብ ተጋርተው በሁለቱ ተሸንፈው ስምንት ነጥቦችን በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት በሲዳማ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ሁለተኛ ድላቸውን ለማሳካት ዛሬ ወደ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በዚህ አመት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ወልዋሎ ዓ/ዩዎች ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ በማሸነፍ በአንዱ ነጥብ ተጋርተው ስድስት ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን አራት ነጥቦችን ብቻ ሰብስበው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል። በስምንተኛው ሳምንት መቀሌ 70 እንደርታ ላይ ያሳኩትን ድል ለመድገም ዛሬ ቀላል የማይባል ፋክክር ይጠብቃቸዋል። ጨዋታውም  ከቀኑ 7:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀኝ መስመር ተከላካዩን ያሲን ጀማልን በቅጣት ምክንያት ከማጣቱ በቀር የተቀሩትን ተጫዋቾች ይዞ የሚቀርብ ይሆናል። ወልዋሎዎች በበኩላቸው በዛሬው ጨዋታ በ8ኛው ሳምንት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣውን ዳዊት ገብሩ በቅጣት እንዲሁም ተከላካዩ ኪም ላም በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ሲችል በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነታቸውም 7 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ንግድ ባንኮች የአራቱ ግብ ባለቤት ሲሆኑ የተቀሩትን ሶስት ግቦች ወልዋሎዎች ማስቆጠር ችለዋል።

አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከቀኑ 9:00 ሲል አዳማ ከተማን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው ጨዋታ ሌላኛው የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብር ነው። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ የተጋሩት አዳማ ከተማዎች አስራ ሶስት ነጥቦችን በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ከሁለት ሽንፈቶች ማግስት በስምንተኛው ሳምንት አርባ ምንጭ ከተማን  በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱትን እና በአስራ አምስት ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ፈረሰኞች ጋር ብርቱ የሆነ የሜዳ ላይ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ያመራው ሚራጅ ሰፋ እና ጋዲሳ ዋዶ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን መጠነኛ ጉዳት ላይ የሚገኙት ቢኒያም ዐይተን እና አሕመድ ሁሴንም ለጨዋታው የመድረሳቸው ነገር እጅግ አጠራጣሪ ነው። በፈረሰኞቹ በኩል አዲሱ አቶላ፣ ሻይዱ ሙስጠፋ፣ ቶሎሳ ንጉሴ እና አሚኑ ነስሮን በጉዳት ምክንያት የማያገኙ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከአርባምንጭ ጋር በነበረው ጨዋታ በአሰልጣኞች ውሳኔ ከጨዋታው ውጭ የሆነው አቤል ያለው ከህመሙ ያገገመ በመሆኑ በዛሬው ጨዋታ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 46 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ 24 ጊዜ ድል ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 61 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው አዳማ ከተማ ደግሞ 34 ግቦችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ 13 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ከዕለቱ ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የምስራቁን ክለብ ድሬዳዋ ከተማን ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያገናኛል። በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት ድሬዎች ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሁለቱ ነጥብ ተጋርተው በቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው አስራ አንድ ነጥብ በመሰብሰብ አስረኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እየተመራ ስድስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በአንዱ ተሸንፈው በተቀረው ነጥብ በመጋራት ሊጉን በአስራ ዘጠኝ ነጥብ እየመሩ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ሲዳማ ቡና አሸንፎ መሪነቱን ያጠናክራል ወይስ ድሬዳዋ ከተማዎች ድል አድርገው ደረጃቸውን ከፍ ያደርጋሉ የሚለው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል። ጨዋታው ቀን 10:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።

ድሬዳዋ ከተማ በአቡበከር ሻሚልን በቅጣት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የማያገኙ ሲሆን መጠነኛ የሆነ ጉዳት ያስተናገደው አስራት ቱንጆ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ሲዳማ ቡና በበኩላቸው በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።

ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ 24 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና 10 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 5 ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል፤ ቀሪዎቹ 9 የእርስ በርስ ግንኙነቶች በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 26 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 18 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሸገር ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የዘጠነኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጨረሻ በሆነው ጨዋታ ሸገር ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ ያገናኛል። በዚህ የውድድር አመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የተቀላቀሉት ሸገር ከተማዎች በዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመሩ በሊጉ ሁለት ጊዜ ድል በማድረግ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻሉ ሲሆን በስምንተኛው ሳምንት ከነገሌ አርሲ ጋር ነጥብ ከተጋሩ በኋላ ሶስተኛ ድላቸውን ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ተጋጣሚያቸው የሆነው ባህር ዳር ከተማም ወጥነት የጎደለው ጅማሮን በሊጉ እያስመለከተን ሲሆን በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እየተመሩ በአስራ ሁለት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከሸገር ከተማ ጋር ፉክክር ያለው ጨዋታን ያስመለክቱናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሸገር ከተማ በኩል የቡድን ዜናን በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በባህር ዳር ከተማ ከጉዳቱ እያገገመ የሚገኘውን ክንዱ ባየልኝን ጨምሮ አጥቂው ዮሐንስ ደረጀ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።