ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ድል አድርገዋል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ድል አድርገዋል

አዳማ ከተማዎች በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፉ ሸገር ከተማዎች ከመመራት ተነስተው ባህር ዳር ከተማን 3ለ1 አሸንፈዋል።

አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

አዳማ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ ገና በመጀመሪያ ደቂቃዎች ግብ ያስመለከተን ሲሆን 4ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ከቀኙ የሜዳ ክፍል ያገኙትን የቅጣት ምት ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማው ሲሆን ሙጅብ ቃሲም ድንቅ የግንባር ኳስ በማስቆጠር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ግቡ ከተቆጠረ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከቆመ ኳስ የተሻማውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቢኒያም ፍቅሬ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ወደ ግብ የመታው ቢሆንም ከግቡ ከፍ ብሎ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጨረሻዎችን ደቂቃዎች ጫናን ፈጥረው በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በሀብታሙ ጉልላት የሳጥን ውጭ ሙከራ ወርቃማ የሚባል ዕድል ያገኙ ቢሆንም ግብ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ፈረሰኞቹ ከሳጥን ውጭ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው አዳማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታን አስመልክተውናል። 71 ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች በነቢል ኑሪ አማካኝነት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በግብጠባቂው ጥረት ወደ ውጭ የወጣ ሲሆን ያንኑ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ሙጅብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ያቀበለ ቢሆንም የአዳማ ተጫዋቾች ሳይደርሱበት የቀረው ኳስ ሁለተኛ ግብ መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። በተጨማሪ ደቂቃዎች አዳማዎች በዳዋ ሆቴሳ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጨዋታው በሙጅብ ቃሲም የግንባር ኳስ አዳማ ከተማዎች 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ሸገር ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የምሽቱ መርሐግብር ከነገሌ ጋር ነጥብ የተጋሩትን ሸገር ከተማ ከድል መልስ ከመጣው ባህር ዳር ከተማ ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውን ተቆጣጥሮ በመጫወት ረገድ ሸገር ከተማዎች የተሻሉ ቢሆንም 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። ብሩክ ሰሙ ከአማካይ ክፍል የሰነጠቀውን ኳስ ኩዋቤና ቧቲንግ አመቻችቶ ለሄኖክ ይበልጣል ያቀበለው ሲሆን ሄኖክም ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ሸገር ከተማዎች የተቆጠረባቸውን ግብ ለማካካስ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግተው የተጫወቱ ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ የባህር ዳሩ ግብጠባቂ በአግባብ አለመያዙን ተከትሎ አቅራቢያው የነበረው ያሬድ መኮንን በቀላሉ ኳስን ከመረብ ጋር ማዋሃድ ችሏል።

የግቡ መቆጠር ወደ ጨዋታ የመለሳቸው ሸገር ከተማዎች በጀቤሳ ሚኤሳ አማካኝነት ለግብ የቀረበ የግንባር ኳስ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶባቸዋል። 65ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳር ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት እንደ መልካም አጋጣሚ ያገኘው አንተነህ ተፈራ ግብን በማስቆጠር ሸገር ከተማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

መሪ መሆንም ከቻሉ በኋላ ደጋግመው ማጥቃታቸውን ያልተውት ሸገር ከተማዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ከመስመር ይዞት የገባውን ኳስ ድንቅ የሚባል የግል ጥረቱን በመጠቀም አሪፍ የሚባል ግብ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ በቡልቻ ሹራ ሌላ ሙከራ ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በሸገር ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።