በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !
ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል
ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል አንዱ የሆነው መርሐግብር ቀን 7፡00 ሲል በ አ/አ ስታዲየም ይካሄዳል።
በፋሲል ከነማ እና በሽረ የተመሳሳይ 1ለ0 ሽንፈት አስተናግደው የመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ደረጃው ወገብ እየተንሸራተቱ ይገኛሉ። ቡድኑ በተለይም ወደ አ/አ ስታዲየም ከመጣ በኋላ ማግኘት ከሚገባው 9 ነጥብ ውስጥ ሦስቱን ብቻ ማግኘቱ ለአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከሜዳው ጋር የሚሄድ አጨዋወት ላይ እንዲያጤኑ የሚጠቁም ነው።
ከድል ጋር ከተራራቁ አራት ሳምንታትን ያስቆጠሩት መቻሎች ካለፉት አራት ጨዋታዎች በአንዱ ተሸንፈው በሦስቱ አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ከሲዳማ ቡና እኩል ከፍተኛ (12) አስቆጣሪ ቢሆንም እያስተናገዳቸው ያሉት ጎሎች (8) መብዛት ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው።
ሀዋሳ ከተማ እስራኤል እሸቱን አሁንም በጉዳት ሲያጣ ሽመልስ በቀለ ደግሞ የዛሬው ጨዋታ በቅጣት ያመልጠዋል። በመቻል በኩል መሐመድ አበራ እና ብሩክ ማርቆስ በጉዳት ኢሞሮ ማናፍ ደግሞ በቅጣት አይኖሩም። ከሦስት ቀናት በፊት ፊርማውን ያኖረው አይቮሪያዊው ተከላካይ ኡራ ከአይ ቲ ሲ እና ሥራ ፍቃድ ጋር የተገናኙ የወረቀት ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው በዛሬው ጨዋታ አይኖርም።
ሁለቱ ቡድኖች 36 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ ከተማ 16 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መቻል 10 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 85 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 47 መቻል በበኩሉ 38 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ነጌሌ አርሲ
በሦስት ነጥቦች ተበላልጠው 12ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በሀዋሳ የሚደረግ ቀዳሚው ጨዋታ ነው።
ወደ ሀዋሳ ካመሩ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ተነቃቅተው የነበሩት ነብሮቹ ከዛ በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ከአርባምንጭ ጋር አቻ ሲለያዩ በኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 1ለ0 ተሸንፈዋል። ቡድኑ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ተቀዳጅቶ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እያለመ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
በተከታታይ ጨዋታዎች ማራኪ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ነጌሌ አርሲ አዳማ እና መድን ላይ ከተቀዳጀው ድል በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ከሸገር ጋር አቻ ሲለያይ በተለይም ቡድኑ ከተለያዩ አማራጮች የግብ ምንጮችን ማብዛቱ ትልቁ ጎኑ ነው። ከሳምንት ሳምንት እየጎለበተ እየሄደ ላለው ቡድን ሦስት ነጥብ አሳክቶ በአሸናፊነት ስነልቦና ለመቀጠል ዛሬ ከሀዲያ ጋር ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፊጮ ፣ ዳግም ንጉሤ ፣ ጄይላን ከማል እና ናትናኤል ሞገስ በዛሬው ጨዋታ አይኖሩም። በነገሌ አርሲ በኩል ኢብሳ በፍቃዱ ከጉዳት ሲመለስ በረከት ወልዴ እና አብዱልባሲጥ ከማል አሁንም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ይህ ግንኙነት ለሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው ነው።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ፋሲል ከነማ
ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል አንዱ የሆነው ጨዋታ 10፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም ይካሄዳል።
በውድድር ዓመቱ ምንም ድል ካላሳኩ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይሄን ያህል የሚያስወቅስ እንቅስቃሴ ባያደርግም ከውጤት አንጻር ግን እጅግ ከፍተኛ መዋዠቅ ላይ ነው። ሆኖም ቡድኑ በቶሎ ወደ ድሎች ካልተመለሰ እንዳለፈው ዓመት የመውረድ ስጋት ፊቱ ላይ ተደቅኖ እየጠበቀው ይገኛል።
በውድድሩ እስካሁን ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ፋሲል ከነማ ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በኋላ ብዙ ስጋቶች በደጋፊዎቹ ዘንድ ቢያድሩም አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የሠሩት ቡድን ግን ከተጠበቀው በላይ ለተጋጣሚዎች ፈታኝ እየሆነ መገኘቱን ቀጥሏል። ሆኖም ቡድኑ ዛሬ ተጨማሪ ድል የሚያሳካ ከሆነ ከመሪው ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ያስችለዋል።
መቐለ 70 እንደርታዎች ጊትጋት ኮች፣ አብርሃም ጌታቸው እና ዮሐንስ ዓፈራን በጉዳት አሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና ቦና ዓሊን ደግሞ በቅጣት አያሰልፉም። ከዚህ በተጨማሪም የዘርኢሰናይ ብርሀነ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው፤ ፍሬዘር ካሳ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በፋሲል ከነማ በኩል ሀብታሙ ተከስተ ፣ ኪሩቤል ዳኜ ፣ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስን በጉዳት እንዲሁም ቃልኪዳን ዘላለም በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱም ቡድኖች የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 6 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታ ላይ ድል አድርገው በተቀሩት 4 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ ሦስት ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
አዞዎቹ እና ቡናማዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።
ካደረጓቸው 8 ጨዋታዎች አራት ተሸንፈው በአራት አቻ ተለያይተው የደረጃው ግርጌ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ከገቡ ሰንበትበት ብለዋል። ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ያለባቸው ጫና በሚታይ መልኩ ማድረግ የሚችሉትን ለማድረግ መቸገራቸው ለአሰልጣኝ በረከት ደሙ ትልቅ ማነቆ ሆኖባቸዋል። ሆኖም ግን አሰልጣኙ አስቸኳይ መፍትሔ ፈልገው ወደ ውጤት መመለስ ትልቁ የቤት ሥራቸው ነው።
ወደ ሀዋሳ ከሄዱ በኋላ በመድን ሽንፈት ቢያስተግዱም ሸገር እና ሀዲያን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የዛሬውን ጨዋታ በመጠነኛ እፎይታ የሚያደርጉ ይሆናል። ቡድኑ ይህንን ጨዋታ አሸንፎ በቀጣይም ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በተሻለ የራስ መተማመን መቅረብ ከአሰልጣኝ ዐቢይ ካሣሁን የሚጠበቅ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ21 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች 8 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ7 ጨዋታዎች ረተዋል። የተቀሩት 6 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል አንዱአለም አስናቀ እና በርናንድ ኦቼንግ አሁንም በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ከሁለቱ በተጨማሪ አማኑኤል ጎበናም በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲታወቅ ጄሮም ፊሊፕ በህመም ምክንያት እንደማይሰለፍ ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ይታገሱ ታሪኩ በጉዳት ምክንያት አይኖርም።


