ሪፖርት | በአ/አ ስታዲየም የተደረጉ የዛሬ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ሪፖርት | በአ/አ ስታዲየም የተደረጉ የዛሬ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረጉ ጨዋታዎች ያለ ግብ ተጠናቅቀዋል።

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው ጨዋታ ጥሩ የሚባል የኳስ ፍሰትን በሁለቱም ቡድን በኩል ያስመለከተን ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ በመውሰድ አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው በተጀመረ በ 4ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ ከአህመድ ሁሴን ተቀብሎ ጎል ለመሆን የቀረበ ኳስ ቢመታም በግብ ጠባቂው ቅልጥፍና ግብ ከመሆን ታድጎበታል። እንዲሁም በ 25ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ሙከራ ግብ ጠባቂው ሞየስ ፓዋቲ በድጋሚ ግብ ከመሆን አድኖታል።

አልፎ አልፎ በረጅም ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በ 30ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ ከጎል ክልል ጠርዝ ላይ ሆኖ የግብ ጠባቂውን መውጣት በመመልከት ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ አጠገብ ወጥቶበታል። ይህም ፋሲል ከነማዎች እጅግ የሚያስቆጭ የግብ ዕድል ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው የአዳማ ከተማው ሀይደር ሸረፋ ከሜዳው የግራ ክፍል የመታው የቅጣት ምት ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጭ ወጥቷል። አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በፍጥነት መድረሱ በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ የተቀዛቀዘ ሲሆን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችም ያለ ሙከራ ያስመለከተን ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል ተቀይሮ በገባው ቢኒያም ጌታቸው አማካኝነት ካደረጉት ሙከራ በስተቀር ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ሳያስመለክቱን ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ በአዳማ ከተማ ስድስተኛ እንዲሁም በፋሲል ከነማ ሰባተኛ አቻ ሆኖ በሊጉ ተመዝግቧል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከመሪዎች ተርታ የሚገኘውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወራጅ ቀጠናው ላይ የተቀመጠውን ወልዋሎ ዓ/ዩ ባገናኘው የዕለቱ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን ሰላሳ ያህል ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኳስ ቁጥጥሩ በመጠኑ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ወደ 3ኛው የሜዳ ክፍል ተጠግተው የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ግን ደካማ ሆነው ተስተውለዋል።

በተመሳሳይ በፈጣን ሽግግሮች ፈጣን የሆኑ የመስመር አጥቂዎቻቸውን ዒላማ ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት ግቦችን ለማግኘት ሙከራ ያደረጉት ወልዋሎ ዓ/ዩዎች በኮንኮኒ ሀፊዝ ሁለት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ነገር ግን በአጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረበ ሙከራን ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሁለቱም ቡድኖች ለሁለተኛው አጋማሽ የሦስት ነጥብ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበትን ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም፤ በኤሌክትሪክ በኩል ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ገብረማርያም ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የያዘበት በወልዋሎ በኩል ደግሞ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ጌትነት ተስፋዬ ከሞከው እና ግብ ጠባቂው ካዳነበት አደገኛ ሙከራ ውጭ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኗቸው ጨዋታው 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።