ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን

በ13ኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተዘጋጅተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በአንድ ነጥብ ተበላልጠው 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ተከታታይ 3 የ0-0 ውጤቶችን ያስመዘገቡት የጣና ሞገዶቹ ዘንድሮ ካደረጓቸው ጨዋታዎች 25% (3) የማሸነፍ 50% (6) የአቻ እና 25% (3) የሽንፈት ፐርሰንቴጆችን ይዘው የውድድር ዓመቱን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየገፉት ይገኛሉ። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ 10 የሊጉ ጨዋታዎች በ7ቱ ምንም ጎል ያልተቆጠረበት ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም የማጥቃት ኃይሉ ግን ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው። አራተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረው የአሰልጣኝ ደግአረገ ቡድን በፍጥነት ወደ ውጤት ተመልሶ በራስ መተማመኑን ካላገኘ ወደ ድል ለመመለስ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሊገባ ይችላል። ከተለያዩ አማራጮች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ የሚገኙት አሰልጣኙ የፊት መስመሩን ማስተካከል የሚጠበቅባቸው ትልቁ ሥራ ነው።

ከ12ቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አራት ድል ፣ አራት አቻ እና አራት ሽንፈት ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ያለፈውን የውድድር ዓመት ሊደግሙት ይመስላል። የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቡድን ሁለቱንም የውድድር ዓመት በከፍተኛ መነሳሳት ቢጀምርም እየቆየ ለብ እያለ እየሄደ ከድል እየራቀ ይገኛል። ከአምስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 ያሸነፉት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻው ጨዋታ በነጌሌ አርሲ ያጋጠማቸው የ3ለ0 ሽንፈት ግን ያልተጠበቀ ነበር። ሆኖም በዛሬው ጨዋታ በተመሳሳይ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ከሚገኝ ቡድን ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ለማሳካት ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማ እንዳሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አስቻለው ታመነ ፣ አቤል አሰበ እና ጀሚል ያዕቆብን እንዲሁም አዲስ ጉዳት ያስተናገደው አብዱልሰላም የሱፍን በጉዳት ሬድዋን ሸረፋን ደግሞ በቅጣት ምክንያት አያገኝም። ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ መሳይ አገኘሁ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ማንያዘዋል ካሳን በዛሬው ጨዋታ አይጠቀምም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን 4 ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ተፈፅመው ባህር ዳር ከተማዎች በ6 ጨዋታዎች ባለድል ሲሆኑ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 2 ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጨዋታዎቹ ባህር ዳሮች 21 እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ 10 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት አልተካተተም)

ኢትዮጵያ መድን ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሳይጠበቁ በደረጃው ግርጌ የሚገኙ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል አንዱ ነው።

በአህጉራዊ ውድድር ከጠንካራው የግብጹ ፒራሚድስ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾችን ቢያጡም በአዲሱ ውድድር ብዙዎቹ ተስፋ እንዲጥሉባቸው አድርገው ነበር። ሆኖም ግን ቡድኑ ቀስ በቀስ ራሱን የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ አግኝቶታል። በተስተካካዩ ጨዋታ ሸገር ከተማን ያሸንፍ እንጂ በመደበኛዎቹ የመጨረሻ 6 ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 18 ነጥብ 3ቱን ብቻ ማሳካቱ የቡድኑን አሁናዊ ሁኔታ በግልጽ ይጠቁማል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በተከታታይ ዓመታት ዝግ ያለ አጀማመር እያደረጉ ወደ ውጤት እንደሚመጡ ቢስተዋሉም የዘንድሮው ውድድር ላይ በተጫዋቾች ተደጋጋሚ ግላዊ ስህተቶች ነጥቦችን እያጣ የሚገኘው ቡድኑ ከዚህ የከፋ የውድድር ጉዞ እንዳያደርግ በቶሎ ወደ ውጤት መመለስ ይኖርበታል።

ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ አርባምንጭ ከተማን አሸንፈው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ምዓም አናብስት ጥሩ ተነሳሽነት ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ የደረጃው ግርጌ ላይ ሲቀመጥ ከፍተኛ ስጋት የነበረባቸው ደጋፊዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ባዩት የኳስ ቁጥጥር እና በተለይም ማራኪ የማጥቃት ሽግግር ተስፋቸውን አለምልመዋል። ሆኖም ግን ዛሬ በተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ኢትዮጵያ መድንን እንደመግጠማቸው ከፍ ያለ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ሰባት ተጫዋቾቻቸውን (አማኑኤል ኤርቦ፣ ዋንጫ ቱት፣ ረመዳን ሁሴን፣ አብዱ ሞሐመድ፣ ታዬ ጋሻው እና ሚሸል ኦቱን በጉዳት እንዲሁም ንጋቱ ገ/ሥላሴን በቅጣት) አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን ለረጅም ወራት ጉዳት ላይ የቆየው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ወደ ልምምድ የተመለሰ ቢሆንም እሱ እና ረመዳን የሱፍ ለዛሬው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሱሌይማን ሐሚድ፣ ቦና ዓሊ፣ ዘርኢሰናይ ብርሃነ እና አማኑኤል ልዑል በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤  ቅጣት እንዲሁም ጉዳት ላይ የነበሩት ጊት ጋትኮች እና ብርሃኑ አዳሙ ግን ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው የውድድር ዓመት ብቻ እርስበእርስ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያውን ጨዋታ 4ለ0 ሁለተኛውን ጨዋታ ደግሞ 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።