መረጃዎች| የ15ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች| የ15ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

15ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ የዕለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

 

 

ሸገር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

 

በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል የሚገኙት ሸገር ከተማዎች ከድል ጋር ከተኳረፉ ሰንበትበት ብለዋል። 3 ድል፣ 5 አቻ እና 6 ሽንፈቶች አስመዝግቦ 14 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ባህርዳር ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ባከናወናቸው ያለፉት ስድስት ጨዋታዎችም ድል ማድረግ አልቻለም። ሸገር ከተማዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ተከታታይ የአቻ ውጤት ማስመዝገብ ቢችሉም ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመራቅ የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ በሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታ ለጠንካራው ተጋጣሚያቸው ሊፈትን በሚችል አኳኋን በመቅረብ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

በ25 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከመሪዎች ጎራ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ከውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈት ለማገገም ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2 – 0 መሸነፋቸውን ተከትሎ ለረዥም ሳምንታት ተቆጣጥረውት የነበረውን የ2ኛ ደረጃ ቦታ በነጌሌ አርሲ የተነጠቁት ዐፄዎቹ ዳግም ወደ ድል ተመልሰው መሪዎቹ ላይ ጫና ለማሳደር በፊት መስመር የሚስተዋልባቸው ጉልህ የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉት ግንኙነት ነው።

 

ነጌሌ አርሲ ከ ወላይታ ድቻ

በድንቅ ግስጋሴ ላይ የሚገኙት ነጌሌ አርሲዎች በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ላይ እያደረጉት ባለው ፉክክር ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ዛሬ ያከናውናሉ። 25 ነጥቦችን ሰብስበው ከመሪው ሲዳማ ቡና በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ሰጎኖቹ አራት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ፈጣን የደረጃ መሻሻል ባሳዩባቸው ጨዋታዎች ላይ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ብቃት በማሳየት ላይ የሚገኙት ሰጎኖቹ መሪው ላይ ይበልጥ ጫና ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ድል ማግኘት ቀዳሚ ዓላማቸው ነው።

 

በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ወላይታ ድቻዎች ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ የመመለስ ዓላማን ሰንቀው ከነገሌ አርሲ ጋር ይፋለማሉ። የጦና ንቦቹ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል። ቡድኑ ካለበት የአደጋ ክልል ወጥቶ ወደ መካከለኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ለመጠጋትም በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህ እንዲሆን ደግሞ ውጤት በማስጠበቅ ረገድ የሚስተዋልበትን ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል። ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ቀድሞ መምራት ቢጀምርም ውጤቱን ማስጠበቅ ተስኖት ነጥብ መጣሉ ይታወሳል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።

 

 

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሽረ ምድረ ገነት

 

17 ነጥቦችን ሰብስበው 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነብሮቹ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መንገድ ተመልሰው ደረጃቸውን ለማሻሻል ሽረ ምድረ ገነትን ይገጥማሉ። ከሳምንታት በፊት ተከታታይ ሦስት ድሎችን በማስመዝገብ አስደናቂ ግስጋሴ ላይ የነበሩት ነብሮቹ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በብዙ ረገድ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የፊት መስመር ማሻሻል ከቡድኑ የሚጠበቅ ቀዳሚው ስራ ነው።

ተመሳሳይ 17 ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ
የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ካደረጓቸው 14 ጨዋታዎች 4 ድል፣ 5 አቻ እና 5 ሽንፈት ማስመዝገብ የቻሉት ሽረዎች በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ከሰንጠረዡ ወገብ እንዲንሸራተቱ ሆኗል። ቡድኑ በ13ኛው ሳምንት ከብልጫ ጋር ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም በተከላካይ ክፍሉ በሚስተዋለው የትኩረት ማነስ እንዲሁም ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ያለባቸው ድክመት አካሄዳቸው ወጥነት የጎደለው እንዲሆን አድርጎታል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፌጮ እና ቃለአብ ውብሸት በቅጣት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን ከጉዳት የተመለሰው ተመስገን ተመስገን ብርሃኑ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ሽረ ምድረ ገነቶች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ውጭ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንዱ በሀድያ ሆሳዕና አንድ ለባዶ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አንዱ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

 

ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ ከጀመሩ በኋላ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መቀዛቀዞች የተስተዋሉባቸው ኤሌክትሪኮች ከመሪዎቹ ላለመራቅ ወደ ድል መመለስ ይኖርባቸዋል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች
ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ከዚህ አካሄድ ለመውጣት ኳስና መረብ ካገናኘ 3 ጨዋታዎችን ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍሉን ማሻሻል ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። ሀምራዊ ለባሾቹ ኢትዮጵያ መድንን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ከመመራት ተነስተው ያስመዘገቡት ድል ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮላቸው የነበረ ቢሆንም በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራታቸው የደረጃ መሻሻል ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በማጥቃቱ ረገድ ተስፋ ሰጪ መሻሻል ማሳየት ቢችልም ከዛሬው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጠንካራውን የኤሌክትሪክ የኋላ ክፍል ሊፈትን በሚችል ብርታት መቅረብ ይጠበቅበታል።

 

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በዛብህ መለዮ እና አብነት ተስፋዬ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በረከት ወ/ዮሐንስ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። እንዲሁም ጉዳት ሊይ የከረመው አብዱላሂ አላዮ ወደ ልምምድ ተመልሷል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ዘላለም አበበ፣ ካሌብ አማንክዋህ እና እንዳለ ዮሐንስ ከጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታው ዝግጁ ቢሆኑም የመሰለፋቸው ነገር በአሰልጣኙ የሚወስን ነው፤: የመስመር ተከላካዩ ያሲን ጀማል ግን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ሆኗል።

 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 36 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። ኤሌክትሪክ 13 አሸንፎ 51 ጎሎች ስያስቆጥር፤ ባንክ 11 አሸንፎ 43 ጎሎች አስቆጥሯል። በ 12 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።