ባሳለፍነው ዓመት ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ወገኔ ገዛኸኝ ወደ በግብፅ ሊያቀና እንደሆነ ሰምተናል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከታዩ ምርጥ አማካዮች መካከል አንዱ የሆነው እና በኢትዮጵያ መድን ከታችኛው ቡድን አንስቶ በዋናው ቡድን ያለፉትን አራት ዓመታት እያገለገለ የሚገኘው አማካዩ ወገኔ ገዛኸኝ የግብፅ ክለብ ጥያቄ ቀርቦለት ዝውውሩ ወደ መጠናቀቁ መድረሱን አውቀናል።
ፈላጊው ክለብ አል ሞካውሎን አል ዓረብ ስፖርት በናስር ከተማ የሚገኝ ከተመሰረተ 53 ዓመታት ያስቆጠረ በዓረብ ኮንትራክተሮች ስር የሚተዳደር ክለብ ሲሆን በግብፅ ፕሪሚየር ሊግ በአስር ነጥቦች በ18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ይገኛል።
ክለቡ ለወገኔ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ውል ያቀረበለት እንደሆነ ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፂዮን መረጃውን አጋርቶናል። የተጫዋቹ ባለቤት አሳዳጊው ክለብ ኢትዮጵያ መድንም በመልካምነት ተጫዋቹ እንዲያቀና ፍቃደኝነቱን እንደገለፀ እና ነገ ለኢትዮጵያ መድን የመጨረሻ ጨዋታውን ሊያደርግ እንደሚችል አውቀናል።
ወገኔ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ካሳለፈው ስኬታማ ቆይታ አንፃር የኮከብ ምርጫ ዕጩ ውስጥ አለመካተቱ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ እንደነበረ ይታወሳል።

