አሰልጣኝ ውበቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ለመውሰድ ጥያቄ አቀረቡ

አሰልጣኝ ውበቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ለመውሰድ ጥያቄ አቀረቡ

በቅርቡ ወደ ደቡብ ሱዳኑ ክለብ ያቀኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ለመውሰድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰምተናል።

አሠልጣኝ ውበቱ ከሳምንታት በፊት ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን ከተስማሙበት የላይቬሪያው ሊከርስ ክለብ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ነገሮች ሊስተካከሉ ባለመቻላቸው ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ሳይጠበቅ ውላቸውን አቋርጠው የደቡብ ሱዳን ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑን ክለብ ጃሙስ ኤፍ ሲን ለሦስት አመት ቆይታ ለማሰልጠን መቀላቀላቸው ይታወሳል።

አሰልጣኝ ውበቱ ከአዲሱ ክለባቸው ጋር የሁለተኛው ዙር ቅድመ ዝግጅታቸውን በታንዛኒያ ካደረጉ በኋላ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታቸውን በድል መጀመራቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ አንድ ኢትዮጵያዊ አጥቂ እርሳቸው ወደ ሚያሰለጥኑበት የደቡብ ሱዳኑ ጃሙስ ለመውሰድ በወኪሉ በኩል ለተጫዋቹ ባለቤት ጥያቄ ማቅረባቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተጫዋቹ የመቻሉ አጥቂ መሐመድ አበራ መሆኑን የሰማን ሲሆን ለሁለት አመት ተኩል ለማስፈረም ጥያቄው ለመቻል ክለብ መቅረቡን ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፅዮን ገልፆልናል። ሆኖም ክለቡ በዚህ ዓመት ሊያሳካ ከሚፈልገው የዋንጫ ግብ አንፃር ጥያቄውን ለመቀበል እንደሚቸገር የክለቡ አመራሮች ማሳወቃቸው የመሐመድ ወደ ጃሙስ የማቅናቱ ነገር ፈታኝ አድርጎታል።

ወኪሉ አዛርያስ እንዳደረሰን መረጃ ከሆነ መሐመድን ወደ ጃሙስ እንዲሄድ ለማድረግ ጥረቱን የሚቀጥል መሆኑን እና በቀጣይ አሰልጣኝ ውበቱ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በተሻለ ክፍያ እንዲሁም አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ወደ ሚያሰለጥኑበት ክለብ ሊወስዱ እንደሚችሉ ለዚህም ትልቅ አክብሮት እንዳለው ነግሮናል።

በመሐመድ አበራ ጉዞ ዙሪያ የሚኖር አዲስ ነገር ካለ የምናሳውቃችሁ ይሆናል።