መረጃዎች | የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች


የመጀመሪያው ዙር የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተስተካካይ ጨዋታ ውጪ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ !

አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በአስራ አንድ ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ከ17 ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ድል በመድገም የነጥብ ልዩነቱን አጥብበው የመጀመሪያውን ዙር ለማጠናቀቅ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። አዞዎቹ በቅርብ ሳምንታት በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት በማሳየት ላይ ይገኛሉ፤ በተለይም በስድስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከወጣ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ላይ የሚገኝ ሲሆን በፋሲል ከነማ ሽንፈት ባስተናገዱበት እንዲሁም በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸው ባስመዘገቡበት ጨዋታ ላይ ያሳዩትን ብቃት ማስቀጠልም ከቡድኑ ይጠበቃል።

በሀያ ሦስት ነጥብ 11ኛ  ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች የሦስት ደረጃዎች መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት አዞዎቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ከስድስት ድል አልባ መርሐ ግብሮች በኋላ ሦስት ነጥብ ያሳኩት ብርቱካናማዎቹ ዛሬ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ ይፋለማሉ። በ11ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ካስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች በኋላ በስድስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኙ ዘልቀው ሀድያ ሆሳዕና ላይ ሁለት ግቦች ያስቆጠሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ዘለግ ካሉ ሳምንታት በኋላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየውን የፊት መስመራቸው ጥንካሬ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

አርባምንጭ ከተማ በጉዳት ምክንያት የሳሙኤል አስፈሪን እና በፍቅር ግዛቸውን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ኤፍሬም ታምራት ደግሞ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ አቤል አሰበ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና አብዲሳ ጀማልን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ቅጣት ላይ የሚገኘው ሄኖክ ሀሰን ብቻ ዛሬ ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጥ መሆኑ ታውቋል።

ቡድኖቹ በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም በእኩሌታ አምስት አምስት ጊዜ  ሲያሸንፉ  4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ 14 ፣ ድሬዳዋ ደግሞ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በሀያ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ የሚያርቃቸውን ድል ፍለጋ ከጦና ንቦቹ ጋር ይጫወታሉ። በ14ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማን ካሸነፉ ወዲህ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከድል ጋር የተራራቁት ቡናማዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመር ጥምረታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

16 ነጥቦችን ሰብስበው 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ነጥባቸውን 19 በማድረስ ሁለት ደረጃዎችን አሻሽለው የመጀመሪያውን ዙር ለማጠናቀቅ ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በ10ኛው ሳምንት ሸገር ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ ወዲህ ድል ማድረግ ያልቻሉት የጦና ንቦቹ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ድል ለማድረግ ይፋለማሉ። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ ከአንዱ ብቻ ሽንፈት ማስተናገዱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ አልቻለም። ከተጠቀሱት ጨዋታዎች ውስጥ ስድስቱን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ቡድኑ ከዚህ አካሄዱ ለመውጣትም እንደ ተጋጣሚው ሁሉ ውጤታማ መሆን ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወቱ ማሻሻል ግድ ይለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። በወላይታ ድቻ በኩል ኬኔዲ ከበደ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን የሙሉቀን አዲሱ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

በ22 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 10 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በቀሪዎቹ ፍልሚያዎች ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ ስድስት ስድስት ጨዋታዎች አሸንፈዋል። በእነዚህ 22 ጨዋታዎች አጠቃላይ 37 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡናማዎቹ 19፤ የጦና ንቦቹ ደግሞ 18 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።