በ16ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና በሱራፌል ተመስገን ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን አሸነፈ
ፋሲል ከነማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ያገናኘው የ16ኛ ጨዋታ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዐፄዎቹ መሪነቱን ተረከብው የመጀመሪያውን ዙር ለመጨረስ ነብሮቹ በበኩላቸው ደረጃቸውን አሻሽለው ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ባደረጉት ፍልምያ ጥሩ ፉክክር ያስመለከት ነበር።

በመጀመሪያው ጨዋታ ምዕራፍ ዐፄዎቹ አንፃራዊ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱበት ቢሆንም አሚር ሙደሲር በአንድ አጋጣሚ ካደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ውጭ በአጋማሹ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ አላደረጉም። በአጋማሹ ዕድሎችን በመፈጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ነብሮቹ ግን ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ብሩክ በየነ ከቆመ ኳስ የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን እና ሞይስ ፖይቴ በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነው ኳስ እንዲሁም ጫላ ተሺታ በፈጣን ሽግግር ሳጥን ደርሳ ብሩክ በየነ ያመቻቻትን ኳስ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ወደ ግብነት ያልቀየራት ወርቃማ ዕድል ነብሮቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ አጋጣሚዎች ናቸው።

በተመጣጣኝ ጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለሰው በሁለተኛው ጨዋታ ምዕራፍ ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ ለመሆን ዕድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው ነብሮቹ ካልተጠበቀ ቦታ ግብ አግኝተዋል። ሱራፌል ተመስገን በቅብብል ሳጥን ደርሳ ከተፈራ አንለይ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት መረብ ላይ ያሳረፋት ግብም ሀድያ ሆሳዕናዎችን መሪ ማድረግ ችላለች።

ከግቡ በኋላ ዐፄዎቹ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት በሙሉ ኃይላቸው ያጠቁበት እና እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችንም ያደረጉበት ነበር። በተለይም ዳግም አወቀ ሳጥን ውስጥ ሆኖ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው የተቆጣጠራት ሙከራ እና ኪሩቤል ዳኜ ከተከላካይ ጀርባ አሻግሯት ቢኒያም ጌታቸው እንደምንም ደርሶ ጨርፏት ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ጨርፎ ያወጣት ለዐፄዎቹ አስቆጪው አጋጣሚዎች ነበሩ። በተቃራኒው ነብሮቹ ነጥቡን አስጠብቀው ለመውጣት በጥብቅ ከተከላከሉ በኋላ ተሳክቶላቸውም ሶስት ነጥብ በማግኘት ደረጃቸውን ከ15ኛ ወደ 10ኛ አሻሽለው የመጀመሪያን ዙር ጨርሰዋል።

