ከደቂቃዎች በፊት ጊኒያዊ የግብ ዘብ ያስፈረመው መቻል አሁን ደግሞ የአጥቂ አማካይ የግሉ አድርጓል።

ከሀገር ውስጥ ያሬድ ካሣዬ፣ አማኑኤል ተርፉ እና ረመዳን የሱፍን በማስፈረም እንዲሁም የነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ የዝውውር መስኮቱን ከቀናት በፊት የተቀላቀለው መቻል አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ውጪ ተጫዋቾች አዙሮ ጊኒያዊውን የግብ ዘብ መሐመድ ካማራን ማስፈረሙን አስነብበናችኋል። ድህረ ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ደግሞ ክለቡ አምስተኛ አዲስ ፈራሚውን ከላይቤሪያ አግኝቷል።
መቻልን የተቀላቀለው ተጫዋች ጄግባይ ሞሪስ ነው። ጥሩ ችሎታ እንዳለው የሚነገርለት የአጥቂ አማካዩ ከዚህ ቀደም በላይቤሪያ የተለያዩ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን ከሀገሩ ወቶም በደቡብ አፍሪካው ቲኤስ ጋላክሲ እንዲሁም ደቡብ ሱዳኑ ጃሙስ ተጫውቷል። በዚህ ሰዓት ተጫዋቹ የጃሙስ ንብረት ሲሆን አሠልጣኝ ውበቱ በክለቡ ሲያሰለጥኑ ብቃቱን በቅርበት ስለሚያቁት ተጫዋቹን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በአንድ ዓመት ውሰት ውል የግላቸው ማድረጋቸው ታውቋል።
ጄግባይ ሞሪስ ከቡድኑ ጃሙስ ጋር በሴካፋ ካጋሜ ካፕ ለመሳተፍ ወደ ሩዋንዳ አምርቶ የነበረው ቢሆንም ክለቡ ከመቻል ጋር የነበረውን ጠንካራ ድርድር በመንተራስ ከመጀመሪያው የሲንጊዳ ብላክስታርስ ጨዋታ ጀምሮ እንዳይጫወት በማድረግ ወደ መቻል የሚያደርገውን ዝውውር እንደፈቀደ ታውቋል።
ጄግባይ ሞሪስ በ2025 ማርች ወር በላይቤሪያ የወቅቱ አሠልጣኝ ቶማስ ኮጆ ጥሪ ቀርቦለት ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል መጀመሩ ይታወቃል። የመቻል አሠልጣኝ የሆኑት ውበቱ አባተም ከተጫዋቹ ጋር ዳግም ተገናኝተው በቀጣዩ የውድድር ዓመት የምንመለከታቸው ይሆናል።

