21ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚካሄድ አንድ ጨዋታ ጅማሮውን ሲያደርግ፤ ጨዋታውን የተመለከተ መረጃ እንደሚከተለው አሰናድተንል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሃ-ግብር ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ ኢትዮጵያ መድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኛል። ኢትዮጵያ መድን በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ አካባቢ በ17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚችለው 15 ነጥብ ውስጥ ማሳካት የቻለው 2 ነጥብ ብቻ መሆኑ (3 ሽንፈት እና 2 አቻ) ቡድኑ ከፍተኛ የማሸነፍ ስነ-ልቦናዊ ጫና ውስጥ መውደቁን ያሳያል።
በተለይም በ20 ጨዋታዎች ያስቆጠረው የጎል መጠን 12 ብቻ መሆኑ የፊት መስመሩ ድክመት በግልጽ የሚታይ ሲሆን ካለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ አለማስቆጠሩ የነገውን ጨዋታ የበለጠ ከባድ ያደርገዋል። መድን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና ካለፉት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም የዛሬውን ጨዋታ ግዴታ ነጥብ የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ ጨዋታው በመከላከል ላይ ያተኮረ ጥንቃቄ እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልት የሚታይበት ሊሆን ይችላል።
በዛሬው ጨዋታ የኢትዮጵያ መድን ተጋጣሚ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባልተረጋጋ የውጤት ጉዞ ውስጥ ሆኖ ወደ ሜዳ ይገባል። ክለቡ በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው 24 ነጥቦችን ብቻ ነው። በተለይም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ አቻ ተለያይቶ፣ በአንዱ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ ድል ማድረጉ (በድምሩ 6 ነጥብ) ቡድኑ ካለው ታላቅ ስም አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑን ያሳያል።

ቡድኑ በሊጉ እስካሁን 16 ጎሎችን አስቆጥሮ 14 ሲቆጠርበት የ+2 የጎል ክፍያ አለው። ይህም የሚያሳየው የተከላካይ ክፍሉ በአንጻራዊነት ጠንካራ ቢሆንም የፊት መስመሩ ላይ ግን የጎል ድርቅ እንደሚታይበት ነው። በእንቅርት ላይ እንዲሉ ደግሞ የቡድኑም የሊጉም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቤል ያለው አለመኖሩ የበለጠ ችግሩን ያገዝፈዋል። ይሁን እንጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመድን ጋር ባለው የታሪክ የበላይነት እና ባለፈው ዙር 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉን እንደ ትልቅ ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ በመጠቀም ዛሬም ለሦስት ነጥብ ከፍተኛ ትንቅንቅ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል የቡድን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አጥቂዎቹ አቤል ያለው እና አዲሱ አቱላ ከቡድኑ ጋር ወደ ሀዋሳ ያልተጓዙ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 30 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 20 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 51 ጎሎች ፣ 3 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረው 7 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

