ሪፖርት | በሀዋሳ የተካሄዱ የዕለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ሪፖርት | በሀዋሳ የተካሄዱ የዕለቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

በሳምንቱ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ  ከ ነገሌ አርሲ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሸገር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ነገሌ አርሲ

የመጀመሪያዎቹን 30 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫ በወሰዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ በፍጹም ጥላሁን አማካኝነት የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከርቀት ሞክሮት እድሪሱ አብዱላሂ እንደምንም ብሎ በያዘው ኳስ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ከ 30 ደቂቃዎች በኋላ ወደ ጨዋታ የተመለሱት ነገሌ አርሲዎች በዘሩባቤል ፈለቀ ሳጥን ውስጥ እና በአለኝታ ማርቆስ ከርቀት በተመታ ኳስ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂው ሻሂኪሎ ፋርክ ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል። አጋማሹም በሁለቱም ቡድን በኩል ግብ ሳያስመለክተን ዜሮ ለዜሮ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ 59ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ነገሌ አርሲዎች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ከቤ ብዙነህ ኢላማውን ማስጠበቅ ተስኖት ወደ ውጭ ወጥቶበታል ይህም ሰጎኖቹ መሪ መሆን የሚችሉበት ወርቃማ እድል ነበር።

የጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ነገሌ አርሲዎች ከቆሙ ኳሶች እና ፈጣን የመስመር አጥቂዎቻቸውን ኢላማ ያደረጉ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ኋላ አፈግፍገው ጥንቃቄ የተሞላበት መከላከልን ምርጫቸው በማድረግ የነገሌን ማጥቃት መመከት የቻሉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው ያለ ግብ አቻ  በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተመጣጣኝ በነበረው ነገር ግን የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ሸገር ከተማዎች በተሻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ  ሸገር ከተማዎች በዮሴፍ ታረቀኝ ሞክሮ የግቡ መስመር ላይ አለን ካይዋ እንደምንም ብሎ ባወጣባቸው፣ በዘነበ ከድር በቋሚው አጠገብ በወጣበት እንዲሁም በቢንያም ፍቅሩ ከሳጥን ውጭ ተመቶ ግብጠባቂው በመለሰበት አጋጣሚ ግቦችን ለማግኘት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በኢትዮጵያ መድን በኩል በብሩክ በላቸው አማካኝነት ከርቀት በሀይል ተመቶ ኢላማውን ባልጠበቀው ኳስ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በሸገር ከተማ በኩል ምስጋና ሚልኪያስ እንዲሁም በመድን በኩል አለን ካይዋ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ የሸገር ከተማው ቡልቻ ሹራ በቀኝ መስመር በጥሩ ተጋድሎ ይዞ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ሜዳ ላይ ተቀይሮ ከገባ አንድ ደቂቃ ብቻ ያስቆጠረው ታዳጊው ዳዊት ካሳው ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ አራተኛው ዳኛ የባከኑ ጭማሪ ደቂቃዎችን በሚያስመለክትበት ወቅት 90+1 ላይ ከግራ መስመር ያሬድ ካሳሁን ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የክለቡ አዲስ ፈራሚ የሆነው ሳሙኤል ሳሊሶ በግንባሩ በመግጨት ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ከመሸነፍ የታደገ ሲሆን የሸገሮችንም ደስታ ከደቂቃዎች ያለፈ እንዳይሆን አድርጓል።