ዛሬ ጅማሮውን ባደረገው የ23ኛ ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሸገር ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ችለዋል

ሸገር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በኳስ እንቅስቃሴ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ሸገር ከተማዎች ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ በ18ኛው እና 30ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅሩ አለማየው በሞከራቸው እና ግብ ጠባቂው በመለሰባቸው የግንባር ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፍጹም ጥላሁን አማካኝነት ለግብ የቀረበ አስቆጪ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ጥረት ግብ ሳይሆን ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሸገር ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 53ኛ ደቂቃ ላይ መነሻውን ከራሳቸው የግብ ክልል ያደረገውና ከተከላካይ ጀርባ ገዛኸኝ ደሳለኝ በረዥሙ ያሻገረውን ኳስ ቢንያም ፍቅሩ አፈትልኮ ከግብ ጠባቂው በላይ ከፍ አድርጎ በመምታት የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሯል::
59ኛው ደቂቃ ላይ ታዳጊው ሚሊዮን ኃይሉ የሸገርን መሪነት ለማጠናከር ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስና ግብ ለማስቆጠር እስከ መጨረሻው በተቻላቸው አቅም ቢታገሉም ጥራት ያላቸውን የግብ እድሎች በመፍጠር ረገድ ተቸግረው ታይተዋል። በመጨረሻም ጨዋታው በሸገር ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ቡና
የመጀመሪያ ግብ ለማስመልከት 14 ደቂቃዎችን ባስጠበቀን ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ሀሰን ሁሴን በጥሩ ሁኔታ ኳስ በመቅጣጠር አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ናትናኤል ዱባለ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በአጋማሹ ቡናዎች ከኳስ ጋር ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል የተሻለ ሙከራ ሳይደረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደ ተጀመረ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል:: የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ያሳዩትን የትኩረት ማጣት ተከትሎ ኳሱን ያገኘው ፓትሪክ ሲቦማና ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል::
ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተጫዋች ቅያሬዎችን ያደረጉት ቡናማዎቹ 60ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሀምዛ ሱልጣን ከቢኒያም ጌታቸው የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ የቻሉበትን ግብ አስቆጥሯል። ቡናዎች የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችሉም በቀሩት ደቂቃዎች የኢትዮ ኤሌክትሪክን ተከላካይ ክፍል አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው 2 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

