ንግድ ባንክ ሁለት ተጫዋቾች ሊያስፈርም ነው

ንግድ ባንክ ሁለት ተጫዋቾች ሊያስፈርም ነው

በአሠልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ ሊቀላቅል ነው።

የካቻምናው የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ በሊጉ ፍልሚያ ነጥቦችን ለመሰብሰብ እየተቸገረ ቢመስልም በት ከትናንት በስቲያ ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 በመርታት ካለበት የስጋት ቀጠና በመውጣት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡደኑ ይበልጥ ራሱን ካለበት ደረጃ ለማሻሻል ደግሞ ሁለት የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የመጀመሪያው ተጫዋች ተከላካዩ አብዱላዬ ዲያክሃም ነው። ሴኔጋላዊው የኋላ ደጀን አብዱላዬ በሀገሩ ክለቦች በዩኤስ ጎሪ፣ አሳክ ድያምቡር፣ ሶናኮስ እና ዩኤስ ኦዋካም የእግርኳስ ህይወቱን የመራ ሲሆን አሁን መዳረሻው ንግድ ባንክ ሆኗል።

ቡድኑን የተቀላቀለው ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የግብ ዘቡ ጊቢ ጆብ ነው። አንድ ሜትር ከዘጠና ስድስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ጋምቢያዊው የግብ ዘብ የአሠልጣኝ በጸሎትን ስብስቡ በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል።

ሁለቱም ተጫዋቾች ነገ አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን በቀጥታ ፊርማቸውን በማኖር በይፋ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።