የሁለቱ ታላቆች ስንብት እና የክለቦቹ መፃኢ እጣፈንታ

የሁለቱ ታላቆች ስንብት እና የክለቦቹ መፃኢ እጣፈንታ

ሁለቱ ግለሰቦች የክለቦቻቸውን ደጋፊዎች ለሁለት የከፈለ ቅቡልነት ቢኖራቸውም ለዓመታት የክለቦቹ ምልክት ነበሩ ፤ አሁን ግን ሁለቱም የሉም ታድያ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ የመዲናይቱ ምልክቶች መፃኢ ጊዜው ምን ይዞላቸዋል?

እግር ኳሳችን ከክቡር ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ በኃላ በምሳሌነት የሚቀርቡ የእግር ኳስ አመራሮችን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ቢመስልም በኢትዮጵያ እግር ኳስ የክለቦች አስተዳደር ውስጥ ከእነዚህ ግለሰቦች በላይ ስም እና ዝና ያለው ግለሰብ ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው ፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስንል እነዚህ ግለሰቦች የክለቡን ስም ተከትለው መምጣታቸው አይቀሬ ነው።

እንደው ፅድቁ ቀርቶ በሚያሰኘው እግር ኳስችን መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ ለ40 ዓመታት እንዲሁም አቶ አብነት ገብረመስቀል ደግሞ ለ24 ዓመታት እጅግ ከፍተኛ ጫና ባለባቸው እና እንደ ዐይን ብሌናቸው የሚሳሱላቸውን ክለቦች በሊቀመንበርነት መርተዋል ፤ አስተዳደራቸው ላይ ምንም እንኳን ብዙ ጥያቄዎች ቢነሳም ለክለባቸው ስላላቸው ፍቅር ግን ማንም ጥያቄ አያነሳባቸውም ሁለቱም ክለባቸውን አብዝተው ይወዳሉ ፤ በአመራርነት በመሩበት ወቅትም ያላቸውን ሁሉ ሳይሰስቱ ሰጥተዋል።

አሁን ላይ ግን ሁለቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዘመናዊ የአስተዳደር ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ስሞች በተለያየ ምክንያት ስልጣናቸውን ለቀዋል ፤ ይህም በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንድ ታሪክ ምዕራፍ መቋጫ እና የሌላ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሮ የተበሰረበት ሆኗል።

መመሰጋገን ብርቁ ለሆነው እግር ኳሳችን አሁን እነዛ ለዘመናት “አምባገነን” ሲባሉ የነበሩት ሁለቱ አመራር እህል ውሃቸው ተቋርጧል። ነገርግን ታሪክ የማይዘነጋቸው ዘመን ተሸጋሪ ሥራዎቻቸው እስወዲያኛው ይወሳል ፤ አቶ አብነት ገብረመስቀል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ካሳኳቸው በርካታ ዋንጫዎች ባለፈ በቢሾፍቱ በሀገራችን እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማን አካዳሚ አስገንብተው ማጠናቀቃቸው ትልቅ አሻራቸው ሲሆን መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ ደግሞ በአንፃሩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ብርሃን የፈነጠቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር እንዲቋቋም ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ትልቁ አበርክቷቸው ነው ፤ ሁለቱ ግለሰቦች ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ቢኖር በየትኛውም እግር ኳሳዊ ስብሰባዎች ላይ የሚያንፀባርቋቸው ከብዙሃኑ የተለዩ ሃሳቦች እና አቋማቸው እንዲሁ መለያቸው ነበሩ።

ያለፉት ጥቂት አመታት ታድያ ሁለቱ ግለሰቦች ለሚመሯቸው የመዲናይቱ ምልክት ለሆኑት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ ፈተና ጉዞ ላይ ነበሩ ፤ በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከ2008 የውድድር ዘመን አንስቶ እያስመለከተን የሚገኘው የኃይል ሚዛን ሽግሽግ ወደ መዲናይቱ ክለቦች አጋድሎ የነበረው የእግር ኳሳችን የኃይል ሚዛን ቀስ በቀስ ወደ ክልል ክለቦች እጅ የመግባቱ ጉዳይ አሁን ላይ የክልል ክለቦች ከፊት ሲመሩ የመዲናይቱ ክለቦች ከከፍተኛ ስጋት ጋር እየታገሉ ህልዋናቸውን ለማስቀጠል እንዲንገዳገዱ አስገድዷቸዋል ከዚህ ባለፈ በተለያዩ እግር ኳሳዊ ባልሆኑ ምክንያቶች ውድድሩ ከመዲናችን መራቁ ክለቦቹ ከደጋፊዎቻቸው እና ከደጋፊዎች ገቢ ማራራቁ ክለቦቹን ይበልጥ ስር ወደ ሰደደ ችግር ያመራቸው ሲሆን እነዚህ ችግሮች አሁን ላይ ገፍተው የክለቦቹን ህልውና እስከመፈታተን በቅተዋል።

ታድያ ይህ ሂደት ክለቦቹን በሜዳ ላይ ውጤት ከመፈተን ባሻገር የክለቦቹን አስተዳደር ወንበር እንዲሁ ስንጥ ሰንብቷል ፤ ችግሮቹ ስር እየሰደዱ ከመሄዳቸው አንፃር መች የሚለው በእርግጠኝነት ባይታወቅም የሁለቱ አንጋፋ አመራሮች ከመንበራቸው የመልቀቅ ጉዳይ ግን አይቀሬ ይመስል ነበር።

በዘመናት ሂደት ዘመኑን የዋጁ አመራሮች እንዲመጡ ቢፈልግም በአቶ አብነት እና መቶ ዓለቃ ፈቃደ ደረጃ ከሁሉም በላይ ክለቡን ያስቀደመ አመራር ማግኘት ግን እጅግ ፈታኝ ነው።

አሁን ሁለቱ ግለሰቦች ሄደዋል ፤ ነገርግን በክለቦቻቸው ለዓመታት በሰሯቸው ስራዎች እተዋሱ ይቀጥላል ነገርግን ቀጣዩ ቁልፍ ጥያቄ እነዚህ ክለቦች ወደየት ያመራሉ የሚለው ጉዳይ ነው። በሀገራችን የተቋማት ግንባታ ታሪክ ውስጥ አብዛኞቹ ተቋማት በመሪዎቻቸው አምሳያ የሚቀረፁ ናቸው በዚህ የተቋማቱ ልብ ምት በመሪዎቻቸው ላይ የተንጠለጠሉ ይሆንና ግለሰቦቹ ዞር ሲሉ ተቋማቱ በወጉ ለመንቀሳቀስ ሲቸገሩ ይስተዋላል የእግር ኳስ ክለቦቻችንም መልክ ከዚሁ የተለየ አይደለም።

እርግጥ ሁለቱም ክለቦች ዕለታዊ ስራን በሚከውን ጽ/ቤት እና በቦርድ የሚመሩ ቢሆንም በየትኛውም የክለቦቹ አስተዳደራዊ እና እግር ኳሳዊ ጉዳዮች ላይ የሁለቱ ግለሰቦች ተፅዕኖ በጣም የጎላ እንደነበር አይዘነጋም ፤ አሁን በድንገት ሁለቱም የሉም ስለዚህ ነገሮች እንዴት ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

ለመጪው አመራር መጪው ጊዜ በፈተና እና በመልካም ዕድሎች የተሞላ ነው በተለይ የክለቦቹን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘውን የፋይናንስ ቀውስ መፍታት ተቀዳሚ የቤት ስራቸው ሲሆን በቀጣይም ተፎካካሪ ቡድንን መገንባት ቀጣዩ የቤት ስራቸው እንደሚሆንም ይጠበቃል።