አንድ ተጫዋች ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆኗል

አንድ ተጫዋች ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆኗል

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከመልሱ ጨዋታ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አንድ ተጫዋች ከጨዋታው ውጭ እንደሆነ ገልፀዋል

በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ውድድር
የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ በከነአን ማርክነህ እና አቤል ያለው ሁለት ግቦች ተጋጣሚው ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ነገው ሁለተኛ ጨዋታ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂው ቢንያም አይተንን በጉዳት ምክንያት አጥቷል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የነገው ጨዋታ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አጥቂው ቢንያም አይተን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጭ እንደሆነ ሲገልፁ ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓት እየተደረገ በሚገኘው የመጨረሻ ልምምድ ላይ እንዳልተገኘም መመልከት ችለናል። አሰልጣኙ ጨምረውም የተቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ቡድናችን በመጀመሪያው ጨዋታ በወላጅ አባቱ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት በጨዋታው ያልተሳተፈው አማካዩ ጋቶች ፓኖም ዳግም ወደ ስብስቡ መቀላቀሉም የሚታወስ ሲሆን አሰልጣኙም ተጫዋቹ ከሳውዲ ዓረብያ አድካሚ ጉዞ በኋላ በቂ ዕረፍት ሳያደርግ በመጀመሪያው ቀን ልምምድ መጀመሩ እንዲሁም በጨዋታው በአካል ባይገኝም ሐዘን ላይ ሆኖም በፅሑፍ መልዕክት በማበረታታት ከቡድኑ ጎን እንደነበር በመግለፅ በተጨማሪም ሐዘኑን ሳይጨርስ ሃገሩን ለማገልገል ብሔራዊ ቡድኑን በመቀላቀል ላሳየው ቁርጠኝነት ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው ገልፀዋል።