ኳስ ፊደሉ፡ ፍስሃ ወልደአማኑኤል ሲታወሱ

ኳስ ፊደሉ፡ ፍስሃ ወልደአማኑኤል ሲታወሱ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን ኮከብ፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን መስራችና የመጀመሪያው ፕሬዚደንት፣ እንዲሁም የበርካታ ወላጅ አልባ ህፃናት አለኝታ የነበሩት አቶ ፍስሃ ወልደአማኑኤል በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ ፍስሃ በሜዳ ላይ ጥበብ፣ ከሜዳ ውጪ በአስተዳደር እና የማህበረሰብ አገልግሎት የማይጠፋ ታሪካዊ አሻራ ጥለው አልፈዋል።

“እኔ ከሐረር እንደመጣሁ መኩሪያ ክለብ (ክቡር ዘበኛ) ነው የገባሁት፤ ከዛ ቀጥሎ የታህሳስ ግርግር በነበረበት ወቅት (1953) ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሁ። ወዲያው ደግሞ ብሔራዊ ቡድን ገባሁ። ከ1955 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫዎችም ተጫውቻለሁ።” ሲሉ ጋሽ ፍስሃ በአንድ ወቅት ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ እግር ኳስ ህይወታቸው ተናግረው ነበር።

ፍስሃ በሜዳ ላይ በነበራቸው የላቀ የኳስ ችሎታ “ኳስ ፊደሉ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለግብ ጠባቂዎች ፈተና በነበረው ጠንካራ የርቀት ምታቸው ምክንያት “መድፈኛው” በመባል ይታወቁ ነበር። ፍስሃ የሀገር ውስጥ ቆይታቸው ረጅም የሚባል ባይሆንም ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድን የላቀ ግልጋሎት ከሰጡ በኋላ በ1961 ዓ.ም. በስኮላርሺፕ እድል ወደ አሜሪካ በማናቅናት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሎስ አንጀለስ (UCLA) ትምህርታቸውን ጀመሩ። ጋሽ ፍስሃ ያንን ታሪካዊ አጋጣሚ በራሳቸው አንደበት እንዲህ ገልፀውታል። “አሜሪካ በ1961 የከፍተኛ ትምህርት እድሉ ደርሶኝ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ (UCLA) ሄድኩ። ወደ አምስት የምንሆን ተጫዋቾች ነን አብረን የሄድነው። በወቅቱ ግማሽ ፕሮፌሽናል ቡድን በሆነው ማካቢ ሎስ አንጀለስ ለሚባል የአይሁዶች ቡድን የመጫት እድል አግኝቼም ነበር።

“ከዛ በኋላ ፕሮፌሽናል ቡድን ሎስ አንጀለስ ውስጥ ሲቋቋም የሎስ አንጀለስ አስቴክስ ቡድን ውስጥ ለመጫወት ችያለሁ። ይህ ደግሞ በልጅነቴ በኋላም ትልቅ ሆኜ ለብሔራዊም ቡድን በምጫወትበት ጊዜ እንደ ሕልሙን እውን እንዲሆን ከምሻቸው ነገሮች አንዱ የነበረው ፕሮፌሽናል ሆኜ የዓለም ቁንጮ ከሆነው ፔሌ እና ልዩ የሆነ የእግር ኳስ ችሎታ ያለው ጆርጅ ቤስት ጋር የመጫወት ህልሜን አሳክቻለሁ። እንዲያውም ከጆርጅ ቤስት ጋራ በሎስ አንጀለስ አስቴክስ ውስጥ አንድ ላይ ተጫውተናል።”

ከእነ ጆርጅ ቤስት ጋር በአንድ ቡድን ከመጫወታቸው ባሻገር፣ ሜጀር ሊግ ሶከር ከመመስረቱ በፊት የሀገሪቱ ትልቅ ሊግ በነበረው North American Soccer League (NASL) ውስጥ ከዓለም ታላላቅ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከነበሩት፦ ፔሌ፣ ፍራንዝ ቤከንባወር፣ ጌርድ ሙለር፣ ኢውዜቢዮ እና ዦአን ክሩይፍ ጋር በባላጋራነት የተጫወቱት ፍስሃ ከስፖርቱ ጎን ለጎን በስኮላርሺፕ እድል ያገኙትን ትምህርታቸውም ከፍ ያለ ደረጃ በማድረስ ከUCLA በባችለር ዲግሪ እንዲሁም ከተለያዩ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎችን አግኝተዋል።

ከትምህርት እና እግር ኳስ ተጫዋችነት ባሻገር ፍስሃ በአስተዳደር ሰውነታቸው ይታወሳሉ። በ1978 ሎስ አንጀለስ ስታርስ የተባለ የኢትዮጵያውያን ቡድን በመመስረት ኢትዮጵያውያን ግንኙነታቸው እንዲጠነክር ከፍተኛ ሚና የተወጡ ሲሆን በ1985 ደግሞ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) እንዲመሰረት ትልቅ አስተዋዕኦ ከማበርከታቸውም በተጨማሪ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል። ለ5 ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚደንትነት ከመሩ በኋላም ከ35 ዓመታት በላይ በበጎ ፈቃደኝነት እና አባልነት አገልግለዋል።

የፍስሃ ወልደአማኑኤል የህይወት መልክ ከእግር ኳስም ይሻገራል። በ1993 ወደ ሀገራቸው በመመለስ ስፖርትን ተጠቅመው ወጣቶችን ከሱስና ካልተገባ መንገድ መጠበቅ እንዲሁም ወላጅ አልባ ህፃናትን መንከባከብ አላማው ያደረገ “አጋር” የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁመዋል። ድርጅቱ ላለፉት 23 ዓመታት ወላጅ አልባና አቅም የሌላቸውን ህፃናት በመደገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።

አቶ ፍስሃ ወልደአማኑኤል በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አልማዝ ጋር ከ50 ዓመታት በላይ በጋብቻ የኖሩ ሲሆን፣ የሁለት ሴት ልጆች አባት እና የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ።

“በጎ ስራ የህይወት ስንቅ ነው!” የሚሉት ፍስሃ ህይወታቸው የእግር ኳስ፣ የትምህርት፣ የአስተዳደር እና የበጎ ሥራ መልክ የነበረው እጅግ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ናቸው። ስማቸውም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል።