ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ሊጉ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መልስ ሲጀምር የሚደረጉ የመጀመሪያ አራት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ባሕር ዳር ከተማ

በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ ሦስት ድሎችን አርባምንጭ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ነጌሌ አርሲ ላይ ያሳኩት ኤሌክትሪኮች የሊጉ መቋረጥ ጥሩ ስሜት ካልፈጠረባቸው ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ድሎች የተገኙት ደግሞ ቀደም ብለው ከተደረጉ 6 ጨዋታዎች በሦስቱ ተሸንፈው በሦስቱ አቻ ተለያይተው ከመጡ በኋላ መሆኑ የሚገኙበትን መነሳሳት እና የማሸነፍ ፍላጎት ለማሰብ አይከብድም። ሆኖም አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የዛሬው ተጋጣሚያቸውም ከድል በመመለሱ ጠንካራ ጨዋታ እንዲጠብቃቸው ሊያደርግ ይችላል።

ከሁለት ሽንፈቶች እና አንድ አቻ ውጤት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ0 አሸንፈው ወደ ዕረፍት ያመሩት የጣና ሞገዶቹ እጅግ በተደጋጋሚ እና አሰልቺ በሆኑ መልኩ በየሳምንቱ እንደሚጠቀሰው ያለባቸው የወጥነት ችግር ማለትም ጠንካራ ጨዋታዎችን አሸንፈው በዛ የመርካት እና ያልተጠበቀ ሽንፈት ማስተናገድን ጨምሮ በእንቅስቃሴ ረገድ ማራኪ አጨዋወት አድርገው በሌላ ሳምንት ፍጹም ተቃራኒ ሆኖ መቅረብን የመሳሰሉት እንከኖች ሊለዩዋቸው አልቻሉም። በዛሬው ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ከ3 ተከታታይ ድሎች በኋላ እንደመምጣቱ በራስ መተማመናቸውን ከፍ ማድረግ የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቀዳሚ ሥራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ የራቀው ሄኖክ ገብረሕይወት በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ባህር ዳር ከተማ አጥቂው ክዋቤና ቦአቲንግን በጉዳት ምክንያት ዛሬ አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው 9 ግቦችን ያስቆጠረው ባሕር ዳር 4 ጊዜ ፤ 3 ግቦችን ያስቆጠረው ኤሌክትሪክ ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ከመጨረሻ 13 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ አሸንፈው በአምስቱ ተሸንፈው በስድስቱ አቻ የተለያዩት እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የማይገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ከነበረባቸው ክፍተት አንጻር ሊጉ ተቋርጦ መክረሙ ጥሩ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ይታሰባል። በሊጉ ሦስተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (25) ያስተናገዱት እና ሦስተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (17) ያስቆጠሩት ብርቱካናማዎቹ በየጨዋታዎቹ እንደ ብልጭታ ከሚያሳዩት የተደራጀ እንቅስቃሴ በኋላ የግብ ዕድሎችን በቀላሉ በማምከን እና ተጋጣሚ ብልጫ እንዲወስድ የተለያዩ ምቹ መንገዶችን በመፍጠር የጨዋታ ቁጥጥራቸውን ሲያጡ ይስተዋላሉ። ይህም በጊዜ ካልተቀረፈ ለአሰልጣኝ ይታገሱ ቡድን አስቸጋሪ ጉዞ ከፊቱ ላይ ተደቅኖበታል።

ከመጨረሻ 7 ጨዋታዎች በሦስቱ አቻ ተለያይተው በአራቱ የተሸነፉት ዐፄዎቹ በውድድር ዓመቱ አስከፊ ጉዟቸው ላይ ይገኛሉ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለዋንጫ ሲፋለም የነበረው ቡድን አሁን የሊጉ ወገብ ላይ ተረጋግቶ ለመቀመጥም በራስ መተማመኑን ያጣ ይመስላል። እንደ ተጋጣሚው ድሬዳዋ ሁሉ ሦስተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (17) ያስቆጠረው ፋሲል ከነበረበት የደጋፊዎች ጉጉት እና የዋንጫ ተፋላሚነት ስሜት የራቀበት ፍጥነት ትልቅ ትኩረት የሚያሻው በመሆኑ አሰልጣኙ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በምን መንገድ ይህንን ፈተና ይሻገሩታል የሚለው የሚጠበቅ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ ሲያም ሱልጣንን በቅጣት ምክንያት ሲያጣ ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ደግሞ በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። በፋሲል ከነማ በኩል ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው አምሳሉ ጥላሁን እና በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ሐብታሙ ተከስተ በዛሬው ጨዋታ የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ቡድኖቹ በሊጉ እስካሁን 17 ጊዜ ሲገናኙ
ድሬዳዋ ከተማ 7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል ከነማ 6 ጨዋታዎች አሸንፏል፤  በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 37 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 21 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 16 ጎሎች አስመዝግበዋል።

 

ሸገር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ድል አሳክተው ደረጃቸውን በማሻሻል ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ያሉት ሸገሮች በመጨረሻዎቹ 12 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ባያጋጥማቸውም ውጤት በማስጠበቁ በኩል የነበረባቸው ክፍተት ተጨምሮ በ9ኙ ጨዋታዎች አቻ መለያየታቸው የደረጃው ግርጌ አካባቢ ላይ አክርሟቸዋል። ሆኖም ፈረሰኞቹን እና ነብሮቹን ሲረቱ የነበራቸው የጨዋታ መቆጣጠር ብቃት ግሩም ነበር። በዛሬው ጨዋታም ከማሸነፍ ውጪ የትኛውንም አማራጭ ይዞ የማይመጣ ተጋጣሚ ከማግኘታቸው አንጻር ጊዜያዊ አሰልጣኙ ኢያሱ መርሐጽድቅ ድላቸውን ለማስቀጥል በምን ዓይነት የጨዋታ መንገድ ይቀርባሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።

በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት እያደረጉ የሚገኙት አዞዎቹ በአዲሱ አሰልጣኛቸው አዲሱ ካሳ መሪነት ካደረጓቸው 7 ጨዋታዎች ሦስት አሸንፈው ፣ ሁለት አቻ ተለያይተው በሁለቱ ሲሸነፉ በእንቅስቃሴ እና በጨዋታ ፍላጎት ረገድ ያሳዩት መሻሻል ግሩም ነው። በተለይም ባሕር ዳር እና አዳማን ሲያሸንፉ የቀረቡበት መንገድ እነዛን ጨዋታዎች ብቻ ላየ ይህ ቡድን የደረጃው ግርጌ ላይ ያለ ነው ቢባል ለማመን የሚከብድ ነበር። ሆኖም ከግርጌው ጫፍ ላይ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ በ8 ነጥቦች ርቀው የተቀመጡት አርባምንጮች ተከታታይ ድሎችን እያስመዘገቡ ወደ ላይ ከፍ ለማለት በአንድ ድል ከመርካት በላይ ትኩረታቸውን ቀጣይነቱ ላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ የመጀመሪያ ሸገር ከተማ 1-0 አሸንፏል።

 

መቻል ከ ሽረ ምድረገነት

ተከታታይ ሦስት ድሎችን አሳክቶ ተሻሽሎ የነበረው መቻል ከዛ በኋላ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች ግን ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው። በወላይታ ድቻ አራት ግቦች ከተቆጠሩበት በኋላ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያልተቆጠረበት መቻል በመከላከሉ ረገድ ካሳየው መሻሻል ውጪ ከእነዚህ ጨዋታዎች በሦስቱ ምንም ግብ ሳያስቆጥር መውጣቱ ትልቁ ድክመቱ ነው። ከነበረበት ተጠባቂነት የተነሳ ውጥረት ውስጥ የገባው የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ቡድን ከመሪው ሲዳማ ቡና በ9 ነጥቦች ከመራቁ አንጻር ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ከማሸነፍ በስተቀር የትኛውም ሌላ ውጤት ከዋንጫ ፉክክሩ በቀላሉ ሊያስቀረው ይችላል።

ቀስ በቀስ ወደ ወራጅ ቀጠናው የወረዱት ሽረዎች ከመጨረሻ 8 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፋቸው ያልተጠበቀ ነበር። በሊጉ ሁለተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (16) ያስቆጠረው ቡድኑ ፊት መስመሩ ላይ የነበረው የሽመክት ጉግሳ ፣ አቤል ማሙሽ እና ዳንኤል ዳርጌን ጥምረት መልሶ በማደራጀት ወደ ድል ካልተመለሰ በራስ መተማመኑን ይበልጥ እያጣ ጫና ውስጥ ከመግባቱ በፊት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐየ አስቸኳይ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።

በመቻል በኩል ከግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ በስተቀር ሌሎች የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ሽረ ምድረ ገነቶች በዛሬው ጨዋታ ሬችሞንድ አይ እና አዲስ ተስፋየን በቅጣት አንተነህ ተስፋየን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው
ሁለቱም በእኩሌታ አንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርጉ 3 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቱ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 8 ግቦችን አስቆጥረዋል።