ሪፖርት| የጦና ንቦቹ ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ ተመንድገዋል

ሪፖርት| የጦና ንቦቹ ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ ተመንድገዋል

ወላይታ ድቻዎች በያሬድ ዳርዛ ብቸኛ ግብ ሽረ ምድረ ገነትን በመርታት ደረጃቸውን አሻሻሉ

ሽረ ምድረ ገነት እና ወላይታ ድቻን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እንዲሁም ሙከራዎች ያልተደረጉበት ቢሆንም የጦና ንቦቹ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ብልጫ ወስደዋል። ያሬድ ዳርዛ ከመስመር አሻግሯት ሳጥን ውስጥ የነበረው ቴዎድሮስ ታፈሰ ወደ ግብነት ያልቀየራት ሙከራ እንዲሁም ቴዎድሮስ ታፈሰ አሻምቷት ኬኔዲ ከበደ በግምባሩ ከገጫት በኋላ ግብ ጠባቂው ያዳናት ዕድል የጦና ንቦቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍም የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች አጋማሹ ጅማሮ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የደረሰችውን ኳስ ወደ ሳጥን ካሻገራት በኋላ መሳይ ሰለሞን ባልተጠቀመባት ዕድል መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት የጦና ንቦቹ በ64ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን መምራት ችለዋል፤ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ ከቀኝ መስመር አሻምቷት ያሬድ ዳርዛ በግምባሩ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ነች።

ከግቡ በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱት ሽረ ምድረ ገነቶችም አቤል እንዳለ አመቻችቷት ዳንኤል ዳርጌ በጥሩ መንገድ ተከላካዮች አታሎ መቷት የግቡ አግዳሚ በመለሳት ኳስ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። ከተጠቀሰው የሽረ ምድረ ገነት ሙከራ በኋላ ወላይታ ድቻዎች ካርሎስ ዳምጠው በግምባሩ ገጭቷት ግብ ጠባቂው እንደምንም ባወጣት እና አቤኔዜር አለማዮህ አክርሮ መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችው አጋጣሚ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በወላይታ ድቻ 1 ለ አሸናፊነት ተጠናቋል።