ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ28ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ28ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች

የ28ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች !

ባህርዳር ከተማ ከ ሸገር ከተማ

በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከአንድ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጨረሻው ጨዋታ በአደም አባስ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት የጣና ሞገዶቹ በአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ከገጠሟቸው ሽንፈቶች በኋላ በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰው ቡድኑ በተለይም በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ያሳያቸው ለውጦች ተስፋ ሰጪ ናቸው፤ በዛሬው ጨዋታም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የታዩ አወንታዊ ለውጦች ማጎልበት ይጠበቅበታል።

በሰላሣ ሁለት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው የሚያርቃቸውን ድል ፍለጋ ባህርዳር ከተማን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው የወጡትና በሊጉ ከነገው ተጋጣሚያቸው ባህርዳር ከተማ በመቀጠል በርካታ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች በወራጅ ቀጠናው መውጫ ላይ ከቆመው ቡድን በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ሆነው በሚያደርጉት የዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ከአቻ ውጤት በላይ ማስመዝገብ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ በማጥቃት ክፍሉ ላይ ያሳየው መሻሻል እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ዛሬ በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ የሚመደበው ባህርዳር ከተማን እንደመግጠሙ የሚገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ይበልጥ መሻሻል ይኖርበታል።

 

በመጀመሪያው ዙር ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የሊግ ጨዋታ ሸገር ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድን

 

በአርባ አንድ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሊጉን መሪ በመከተል ከሚገኙ ክለቦች በነጥብ ለመስተካከል የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። በመጨረሻው መርሐ ግብር አዳማ ከተማን በማሸነፍ ዳግም ወደ ድል የተመለሱት ኤሌክትሪኮች በቅርብ ሳምንታት የሚታይ ለውጥ ካመጡ የሊጉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። በመሀል በቅዱስ ጊዮርጊስ ከገጠመው ሽንፈት ውጭ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አራት ድሎች እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ በያሬድ የማነ ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማን በረታበት ዕለት በመከላከልና ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ የነበሩበትን አወንታዊ ጎኖች ማስቀጠል እንዲሁም በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ቅርብ ሳምንታት ውስን መቀዛቀዝ የታየበትን የፊት መስመሩ ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅበታል።

 

በሰላሣ ነጥብ ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች ነጥባቸውን 33 አድርሰው ከአደገኛው ቀጠና መውጣት የሚችሉበትን ድል ለማስመዝገብ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይፋለማሉ። የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ መድኖች ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ውጤት መመንዘር ተቸግረዋል። ቡድኑ ጠንካራ ቡድኖችን በገጠመባቸው የቅርብ ሳምንታት ጨዋታዎች በሁሉም ረገድ የተሻለ ብልጫ መውሰድ ቢችልም የግብ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ያለበት ድክመት ነጥብ እንዲጥል አስገድዶታል። በትኩረት ማነስ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ግብ ባስተናገዱበት የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ እንዲሁም ከነጌሌ አርሲ ጋር ባደረጉትና በርካታ የግብ ዕድሎች በፈጠሩበት ጨዋታ ላይ የተስተዋሉባቸው የአፈፃፀም ክፍተቶች ማረምም ከቡድኑ ይጠበቃል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሀብታሙ ሽዋለም እና ቢንያም በቀለ ከቅጣት ሲመለሱ በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ሄኖክ ገብረመድህን ግን አሁንም ቡድኑን አያገለግልም። በኢትዮጵያ መድን በኩል ዋንጫ ቱት፣ ንጋቱ ገብረስላሴ እና በረከት ካሌብ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች 29 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 16 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን 8 ጨዋታዎችን አሸንፏል። በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ለወትሮውም በጎል የታጀበ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ጨዋታዎች 2 ጊዜ ብቻ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ኤሌክትሪክ 43 ፣ መድን 28 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

 

ሽረ ምድረ ገነት ከ ወላይታ ድቻ

ሀያ ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ ከነገው ተጋጣሚያቸው በሁለት ነጥብ እና አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካሸነፉበት የ21ኛው ሳምንት መርሐ ግብር በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ሽረ ምድረ ገነቶች ውጤቱን ተከትሎ ወራጅ ቀጠናው ላይ ተቀምጠዋል። የመጀመሪያው ዙር በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ 12ኛ ሆኖ ካገባደደ በኋላ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ማስመዝገብ የቻለው ቡድኑ ወደ ቀድሞ ብቃቱ ዳግም ለመመለስ በቂ የግብ ዕድሎች እየፈጠረ የማይገኘው የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ለውጦች ማድረግ እንዲሁም የተጋጣሚው ፈጣን የመልሶ ማጥቃቶች መግታት ግድ ይለዋል።

 

በሰላሣ አንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከፍ ያለ የደረጃ መሻሻል ሊያስገኝላቸው የሚችል ድል ለማግኘት ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር ይፋለማሉ። በሰባት የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ በፋሲል ከነማ አንድ ለባዶ የተረቱት የጦና ንቦቹ ዛሬ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እያደረጉት ባለው ፍልሚያ ወሳኝ የሆነ ጨዋታ ያከናውናሉ። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ርቀት የሚገኘው ቡድኑ ዛሬ የሚያሸንፍ ከሆነ ነጥቡን ሰላሣ አራት አድርሶ በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከተቀመጡ ክለቦች ጋር በነጥብ ይስተካከላል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ በመልሶ ማጥቃቶች ላይ ጥገኛ የነበረውን የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ተጋጣሚው በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ካሳየው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅበታል።

የተሰረዘውን እና በሽረ ምድረ ገነት የሁለት ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር 5 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ በአራቱ ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ አሸንፏል። በጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 4 ሽረ ምድረ ገነት ደግሞ 3 ግብ አስቆጥረዋል።