የ29ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ ፍልሚያዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል

ሀድያ ሆሳዕና ከ መቐለ 70 እንደርታ
ሀዲያ ሆሳዕና በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወደ ሜዳ ሲገባ ቀድሞ በተመራባቸው ያለፉትን ሁለተ ጨዋታዎች እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ተፋልሞ ነጥብ ይዞ መውጣት መቻሉ ወቅታዊ ጥንካሬው ነው። ቡድኑ በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተዋጣለት ቢሆንም የተገኙ የግብ ዕድሎች ተጠቅሞ ግጥሚያዎችን ቀድሞ የመጨረስ ድክመቱ ለተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች ዳርጎታል። በ28 ጨዋታዎች 10 ጊዜ ነጥብ መጋራቱ የፊት መስመሩ ካለው የፍጥነት ጥራት ጋር የሚመጣጠን ውጤት እያመጣ አለመሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ዛሬም ይህንን ክፍተት ካላረመ ለድል መብቃቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
በሌላ በኩል መቐለ 70 እንደርታ በደረጃ ሰንጠረዡ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ ወደ ዛሬው ፍልሚያ ይገባል።
ቡድኑ የውድድር ዓመቱን አብዛኛውን ጊዜ በሽንፈትና በአቻ ውጤት ሲያሳልፍ ቢቆይም በቅርብ ሳምንታት ግን አስገራሚ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ማሳካቱም የዚህ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚው መቐለ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የዛሬው ጨዋታ የሞት ሽረት ትግል ነው። ምንም እንኳ በተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች አሁንም ስጋት ቢሆኑም በቅርብ ጨዋታዎች ያሳየው ግብ የማስቆጠር ብቃት ግን ለሀዲያ ሆሳዕና ተከላካዮች ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። ዛሬ የሚያገኘው ድል ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ አምልጦ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመጠጋት ወሳኝ ምዕራፍ ይሆንለታል።
ቡድኖቹ በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስቱ በ 3 ድል ሲቀናቸው ነብሮቹ 2 ጨዋታ አሸንፈዋል። መቐለ 70 እንደርታ 6 ግቦች ሲያስቆጥር ሀድያ ሆሳዕና 4 አስቆጥሯል።
ነገሌ አርሲ ከ ፋሲል ከነማ
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ብርቱ ፉክክር እያደረገ የሚገኘው ነገሌ አርሲ በ28 ጨዋታዎች 44 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዛሬውን ወሳኝ ጨዋታ ይጠባበቃል። ቡድኑ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች 6 ነጥብ (1 ድል፣ 3 አቻ እና 1 ሽንፈት) ያስመዘገበ ሲሆን በተለይም በተከታታይ ሶስት ሳምንታት ነጥቦችን በአቻ ውጤት መጋራቱ ከመሪው ሲዳማ ቡና ያለውን የ10 ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የሚያደርገውን ጉዞ ፈታኝ አድርጎበታል። የነገሌ አርሲ ዋነኛ ጥንካሬ በሊጉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውና በ28 ጨዋታዎች 20 ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ጠንካራ የተከላካይ ክፍሉ ቢሆንም በዛሬው ጨዋታ የፊት መስመሩ ወደ ቀድሞ ብቃቱ ካልተመለሰ ግን ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ መቸገሩ አይቀሪ ነው።
በሌላ በኩል በ42 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ዛሬ ነገሌ አርሲን ማሸነፍ ከቻለ በደረጃ ሰንጠረዡ ተጋጣሚውን በልጦ እስከ 2ኛ ደረጃ የመውጣት ሰፊ ዕድል አለው። ፋሲል ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 8 ነጥብ (2 ድል፣ 2 አቻ እና 1 ሽንፈት) በመሰብሰብ በአንጻራዊነት የተሻለ ግስጋሴ ላይ ይገኛል። የዐፄዎቹ ጥንካሬ በመከላከል እና በማጥቃት መካከል ባለው ሚዛናዊ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በ28 ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው 19 ግቦች ብቻ መሆናቸው ግን የቡድኑን የማጥቃት አቅም ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው። ፋሲል ከነማ ባለፈው ሳምንት በመቐለ የደረሰበትን የ3-0 ሽንፈት አገግሞ ዛሬ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ብርቱ ትግል ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ጨዋታ ነገሌ አርሲ የሁለተኛ ደረጃ ተፎካካሪነቱን ለማጠናከር ፋሲል ከነማ ደግሞ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለመቀላቀል የሚያደርጉት ፍልሚያ በመሆኑ በሁለቱም ወገን ጥንቃቄ የታከለበትና በመሃል ሜዳ የበላይነት ላይ ያተኮረ የታክቲክ ትግል የሚታይበት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አንድ ጊዜ መገናኘት የቻሉ ሲሆን ፋሲል ከነማ 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
አርባ ምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አርባ ምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል ዛሬም ይቀጥላል። ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ቢቀመጥም ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከጠንካራ ክለቦች ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ የተከላካይ ክፍሉ መሻሻል ማሳየቱን ያመላክታል። ዛሬ የሚደረገው ጨዋታ ለአርባ ምንጭ ከተማ እጅግ ሲሆን በ28 ጨዋታዎች 34 ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍሉም መሻሻል የሚገባው ነው። ዛሬ ድል ካደረገ ከፊት ካሉ ተቀራራቢ ነጥብ ካላቸው ቡድኖች ጋር ያለውን ልዩነት የሚጠብበት ዕድል የሚሰጠው እንደመሆኑም በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በተቃራኒው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወቅታዊ አቋሙ ላይ ትልቅ ጥያቄ ምልክት ተጋርጦበታል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ በተለይም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ነጥብ መጣሉ በ12ኛ ደረጃ ላይ እንዲረጋ አድርጎታል። የቡድኑ ዋነኛ መሣሪያ የሆነው 35 ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት መስመሩ አሁንም ተጠባቂ ቢሆንም የተከላካይ ክፍሉ በተመሳሳይ 35 ግቦችን ማስተናገዱ ግን በቡድኑ ውስጥ ያለውን የመከላከል መዋቅር ድክመት ያሳያል። ለንግድ ባንክ የዛሬው ጨዋታ የውጤት መንገጫገጩን ለመግታትና ወደ መረጋጋት ለመመለስ ትልቅ ዕድል ነው።
በአጠቃላይ ጨዋታው በነጥብ የተራራቁ ቡድኖችን ቢያገናኝም ሁለቱም ግን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት የሚያደርጉት ፍልሚያ ስለሚሆን ሜዳው ላይ ብርቱ ፉክክር እንደሚታይ ይገመታል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 15 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ በ3 ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል በተቀሩት 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ንግድ ባንክ 20 ግቦች፣ አርባምንጭ 17 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ቡናማዎቹ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ቀንቷቸው በሁለቱ አቻ በመለያየት ያለመሸነፍ ጉዟቸውን አጠናክረዋል። በተለይም ባለፈው ሳምንት በፈረሰኞቹ ላይ ያስመዘገቡት የ3-1 ድል ቡድኑን በከፍተኛ ስነ-ልቦና በራስ መተማመን ላይ እንዲገኝ ያደርገዋል። የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ብቃቱ ሲሆን በ28 ጨዋታዎች 31 ግቦችን ማስቆጠሩም የዚሁ ማሳያ ነው። ሆኖም አልፎ አልፎ የሚታይበት የነጥብ መጋራት አዝማሚያ እና በመከላከል ረገድ የሚታዩ የትኩረት ማጣት ክፍተቶች እንደ ደካማ ጎን የሚጠቀሱ ስጋቶቹ ናቸው።
በተቃራኒው ወልዋሎ በ32 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋል። ቡድኑ ወጥ የሆነ የውጤት መረጋጋት ባይኖረውም በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ ያለው አቀራረብ እንደ ትልቅ ጥንካሬ ይነሳለታል። በተለይም በኢትዮጵያ ዋንጫ መቻልን በሊጉ ደግሞ ንግድ ባንክን ያሸነፈበት መንገድ ትላልቅ ቡድኖችን የመፈተን አቅም እንዳለው ማሳያ ነው። ሆኖም በ28 ጨዋታዎች 28 ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍሉ እና ማስቆጠር የቻላቸው 22 ግቦች ብቻ መሆናቸው ቡድኑ በሁለቱም የሜዳ ጫፎች ላይ ያለበትን ክፍተት እንደ ደካማ ጎን ያሳያል። ለወልዋሎ ዛሬ ነጥብ ማግኘት ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርገውን የህልውና ትግል አስተማማኝ ያደርግለታል።
የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 7 ጊዜያት የተገናኙት ቡድኖቹ ኢትዮጵያ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አንድ ጨዋታ ወልዋሎ ድል ሲያደርግ 3 ጨዋታዎችን አቻ ተለያይተዋል። ቡና 5 ግብ ሲያስቆጥር ወልዋሎ 3 አስቆጥሯል።

