መቻል ከመሪው ጋር ያለውን ነጥብ ማጥበብ የሚችልበትን አጋጣሚ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ በመጋራት ሳይጠቀም ቀርቷል።

በቀን አስር ሰዓት ሲል በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ የተደረገው ብቸኛ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከመቻል አገናኝቷል። የጠራ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችኝ ማድረግ ችለዋል፤ በተለየም 29ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ማርቆስ ከኮሊንስ ኮፊ የተሰነዘረውን አደገኛ ሙከራ የመለሰበት አጋጣሚ ይታወሳል።
በአጋማሹ አምብዛም የግብ ማግባት አጋጣሚ ያልፈጠሩት አዳማዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አሊዋንዜ የተቆጣጠረበት ኢላማውን የጠበቀ አደገኛው ሙከራ ሲጠቀስ አጋማሹም ግብ ሳይቆጠረብት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ በመቻሎች ኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተመለሰው በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሆነው ቀዳሚ ለመሆን ተጋጣሚው መፈተን የቻሉ ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከቸርነት ጋር ተቀባብሎ ግብ ጠባቂው መውጣቱን አይቶ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ከቀረው ሙከራ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ ረዘም ላለ ደቂቃ አስቆጪ የሚባል ሙከራም እንዲሁም አጋጣሚዎችን ሳይፈጥሩ ቆይተዋል። በመጨረሻዎች አስር ደቂቃዎችም ኮሊንስ ኮፊ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣበት ሙከራ አይዘነጋም።
በተቃራኒው በግራ መስመር ሰብረው በመግባት እንዲሁም በመልሶ ማጥቂት ግቦችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዳማ ከተማዎች የነበሩ ቢሆንም የመቻልን የተከላካይ መስመር አልፈው ግልፅ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፣ ሆኖም ግን በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ቢኒያም አይተን አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚ ሲታወስ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀየሮ የገባው ማይክል ኪፕሩቪ በቀኝ መስመር ገብቶ ፈቱዲን ጀማል ያስጣለለው አደገኛው አጋጣሚ በመጨረሻ ደቂቃ ሶስት ነጥብ ሊያስገኛቸው የቀረበ አስቆጪው አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

