ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ድል ሲቀናው ሀዋሳ ከተማ እና ሸገር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ድል ሲቀናው ሀዋሳ ከተማ እና ሸገር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ጅማሯቸውን ሲያደርጉ የጦና ንቦቹ ወደ ድል ሲመለሱ ሀዋሳ ከተማ እና ሸገር ከተማ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የ30ኛው ሳምንት ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ በሆነውና ተቀዛቅዞ በጀመረው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በቴዎድሮስ ኃይለማርያም አማካኝነት ተከታታይ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተው በ40ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ መልካሙ ቦጋለ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በመከላከል ላይ የተመሰረተ የመልሶ ማጥቃት ስልትን ምርጫቸው ሲያደርጉ ሀድያ ሆሳዕናዎች ቡበኩላቸው በፈጣን መስመር አጥቂዎቻቸው አማካኝነት የአቻነት ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የድቻን የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ሳይቻላቸው ቀርቷል።

በአጠቃላይ ሆሳዕናዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም የጦና ንቦቹ በመከላከል ረገድ በነበራቸው ጥንካሬ ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በወላይታ ድቻ የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሸገር ከተማ

በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ግብ የማስቆጠር ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻለ የበላይነት ማሳየት የቻሉ ሲሆን በተለይም ተባረከ ሄፋሞ እና ብሩክ ታደለ ከሳጥን ውጭ አክረው በመቷቸው ኳሶች የሸገርን የግብ ክልል በእጅጉ መፈተን ችለው ነበር።

የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ሀዋሳዎች ከርቀት ባገኙት የቅጣት ምት ብሩክ ታደለ የመታውን ኳስ የሸገሩ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ሊቆጣጠረው ሲሞክር ከእጁ አምልጦ መረብ ላይ በማረፉ ሀዋሳ ከተማዎች ጨዋታውን 1 ለ 0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሸገር ከተማዎች በቁጥር በዝተው በማጥቃት የጨዋታውን ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን ይህም ግፊታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች በፈጠሩት ቅንጅት አቻ መሆን ችለዋል። ሚሊዮን ኃይሉ በግንባሩ ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ ታዳጊው ይስሐቅ ገብረኢየሱስ ከተከላካዮች ጀርባ ፈጥኖ በመውጣት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ይህንን ውጤት ተከትሎ ሀዋሳ ከተማዎች ለተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች መሪነታቸውን ማስጠበቅ የተሳናቸው ሲሆን ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።