የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት በ35 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስመዘገበው ውጤት (1 ድል፣ 1 አቻ እና 3 ሽንፈት) ወቅታዊ አቋሙ መውረዱን በግልጽ ያሳያል። ከሙያዊ ታክቲክ አንፃር የቡድኑ ዋና ጥንካሬ በሊጉ ካሉ ክለቦች የተሻለ ግብ የማስቆጠር ብቃት (35 ግቦች) ያለው መሆኑ ቢሆንም በተቃራኒው ደግሞ በ29 ጨዋታዎች 35 ግቦችን ማስተናገዱ የተከላካይ ክፍሉ የአደረጃጀት ችግር ያለበትና ለተጋጣሚ አጥቂዎች ክፍተት የሚሰጥ መሆኑን ያረጋግጣል። በተለይ ከመስመር የሚነሱ ኳሶችን በመከላከል ረገድ የሚታይባቸው ድክመት ለነገው ጨዋታ ትልቅ የቤት ስራ እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል።
በሌላ በኩል በ36 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል 2 አቻ እና 2 ሽንፈት በማስመዝገብ ወጥ ያልሆነና ደካማ ጉዞ እያሳለፈ ይገኛል። የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ በአንጻራዊነት አነስተኛ ግብ (27 ግቦች) የተቆጠረበት የተከላካይ መስመር ያለው መሆኑ ቢሆንም የማጥቃት ክፍሉ ግን በ29 ጨዋታዎች 24 ግቦችን ብቻ በማስቆጠሩ የጎል ድርቅ ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል። ይህ የማጥቃት ድክመት ነገ ከንግድ ባንክ ተከላካይ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ውጤት ለመቀየር ዋነኛው ፈተናቸው ሊሆን ይችላል። ሁለቱም ቡድኖች ካላቸው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ጨዋታው ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር እንደሚሆን ይጠበቃል።
ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው 40 ያህል ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 25 አሸንፎ ፣ በ11 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 4 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 72 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 24 ጎሎች አስቆጥረዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ግብ ጠባቂው ጊቤ ጁቤ በቅጣት ምክንያት የማይኖር ሲሆን ጉዳት ላይ የሰነበተው አዲስ ግደይ ምንም እንኳን ልምምድ ቢጀምርም ለዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሊጉ መካከለኛ ስፍራ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከምስራቁ ቡድን ድሬዳዋ ከተማ ጋር ይፋለማል። ኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት በ41 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ለመራመድ የሚያደርገውን ጉዞ ገትቶታል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በወልዋሎ ዓዲግራት የደረሰበት የ4 ለ 2 አስደንጋጭ ሽንፈት የኋላ ክፍሉ ላይ ያለውን ክፍተት ያጋለጠ ቢሆንም በሊጉ 33 ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት መስመሩ ግን ዛሬም ለተጋጣሚው ስጋት መሆኑ አይቀርም። ቡናማዎቹ ከሽንፈቱ መልስ በፍጥነት ወደ ድል ለመመለስና ያላቸውን የ0 የግብ ልዩነት በማሻሻል ወደ መጀመሪያዎቹ አምስት ደረጃዎች ለመጠጋት ዛሬ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ33 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካለው የነጥብ ጥበት አንጻር የዛሬው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመራቅ ወሳኝ ነው። ድሬዳዋ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት የገጠመው ሲሆን በተለይም ባለፈው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 1 ለ 1 አቻ መለያየቱ ነጥብ የማስጠበቅ ክፍተት እንዳለበት አሳይቷል። የቡድኑ ዋነኛ ድክመት በ29 ጨዋታዎች 30 ግቦችን ያስተናገደውና በሊጉ ከፍተኛ የግብ ዕዳ (-10) ካለባቸው ቡድኖች አንዱ መሆኑ ነው። ሆኖም ድሬዳዋ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ያለው ጠንካራ ተከላካይ እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለኢትዮጵያ ቡና በቀላሉ እጅ የማይሰጥ ያደርገዋል። ብርቱካናማዎቹ ዛሬም የፊት መስመራቸው ላይ ያለውን የግብ ድርቀት በመቅረፍ ካልተጫወቱ የሊጉ መቆያ እድላቸው በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ እንዲንጠለጠል ሊገደዱ ይችላሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 27 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 15 በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ይዟል። 6 ጨዋታ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ 6 ጨዋታ አሸንፏል። ቡናማዎቹ 45፣ ብርቱካናማዎቹ 26 ጎሎች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)

መቐለ 70 እንደርታ ከ አርባምንጭ ከተማ
በሊጉ ለመቆየት የሚደረገው የመኖር ወይም አለመኖር ፍልሚያ ዛሬ ምዓም አናብስትን ከ አዞዎቹ ያገናኛል። ሁለቱም ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጠው የሊጉን ቆይታቸውን ለማረጋገጥ የዛሬው ጨዋታ የስድስት ነጥብ ያክል አስፈላጊ ነው።
መቐለ 70 እንደርታ ዛሬ ወደ ሜዳ ሲገባ በ30 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነው። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት በአንዱ ነጥብ በመጋራት በሁለቱ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባለቀ ሰዓት በተቆጠረበት ግብ ምክንያት 1 ለ 1 አቻ በመለያየቱ ቁጭት የሚፈጥር የጨዋታ ሳምንት ያሳለፉ ሲሆን ባደረጓቸው በ29 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 21 ግቦች ብቻ መሆናቸው የማጥቃት መስመሩ የዛሬውን ወሳኝ ጨዋታ ለማሸነፍ ያለበትን ትልቅ የቤት ስራ ያሳያል። በተለይም በሊጉ ካስተናገዳቸው 31 ግቦች አንጻር ያለው የ-10 የግብ ዕዳ ቡድኑ ዛሬ ከኋላ ክፍሉ ጥንካሬ በላይ የፊት መስመሩን ችግር የመቅረፍ ግዴታ እንዳለበት ይጠቁማል።
አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በ25 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ተቆጣጥሮ ይገኛል። አዞዎቹ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን በአቻ ውጤት በመለያየት እና አንዱን በመሸነፍ የድል ረሃብ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየቱ የተከላካይ ክፍሉ መሻሻልን ቢያሳይም በ29 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 21 ግቦች ግን ካለበቶት ደረጃ ጋር ተደምሮ ትልቅ ጫና ውስጥ ከቶታል። አርባምንጭ በሊጉ ካስተናገዳቸው 34 ግቦች አንጻር ያለው የ-13 ከፍተኛ የግብ ዕዳ ዛሬም ለተጋጣሚው ጥቃት ተጋላጭ ሊያደርገው ይችላል።
ቡድኖቹ በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስት 3 ጊዜ ድል ሲያደርጉ በ2 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱ መቐለ 9 ግቦች ሲያስቆጥር አርባምንጭ 2 ግቦች አስቆጥሯል።
መቐለ 70 እንደርታዎች አሁንም የአሸናፊ ሀፍቱን ግልጋሎት አያገኙም፤ በተጨማሪም የቦና ዓሊ መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን ኮትዴቭዋራዊው አብዱለጢፍ ባምባ ግን ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ለነገው ፍልሚያ ዝግጁ ሆኗል።
ምድረገነት ሽረ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ለምድረገነት ሽረ ከእንግዲህ የሚኖሯቸው ጨዋታዎች የዛሬውን ጨምሮ ከወራጅ ቀጠናው አረንቋ ለመውጣት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው። ምድረገነት ሽረ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ካደረገ 67 ያክል ረጅም ቀናትን አስቆጥሯል። ካለፉት 8 ጨዋታዎች በአንዱም ድል ቀንቶት የማያውቀው ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በ30 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ ካስቆጠራቸው 18 ግቦች አንጻር የአጥቂ ክፍሉ ግብ አለማስቆጠር በዛሬው ጨዋታ ላይ ትልቅ ጥላ ማጥላቱ ባይቀርም የ67 ቀናቱን የድል ርሃብ ለመስበር የሚኖረው መነሳሳት ለኤሌክትሪክ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል።
በተቃራኒው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወደ ላይኛው ክፍል የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሁኑ ወቅት በ42 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት በእጅጉ እየተቸገረ ይገኛል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለቱ ነጥብ የተጋራው ኤሌክትሪክ ባለፈው ሳምንት በመቻል 1 ለ 0 መሸነፉ ወዱ መሪዎች የመጠጋት ስራውን አክብዶበታል። ቡድኑ በ29 ጨዋታዎች 22 ግቦችን በማስቆጠር ውጤታማ የማጥቃት መስመር እንዳለው ቢያሳይም በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የመጣል አባዜው ግን ዛሬም ስጋት ይሆንበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች ቀደም ሲል በሊጉ ሶስት ጊዜ ብቻ የተገናኙ ሲሆን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀዳጅ በቀረው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪኮች ሁለት ግብ ሲያስቆጥሩ፣ ሽረዎች ግን በግንኙነታቸው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።
በሽረ ምድረገነቶች በኩል ክፍሎም ገ/ህይወት እና ቢንያም ላንቃሞ ከጉዳታቸው አገግመው ለዛሬ ጨዋታ ይደርሳሉ፤ ሽመክት ጉግሳ ግን አሁንም በቅጣት ምክንያት ቡድኑን አያገለግልም።

