32ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በሰላሣ ስድስት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ካሉበት የስጋት ቀጠና የሚያርቃቸውን ዳ ፍለጋ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታሉ።
ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ካስገኙላቸው ሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በእኩሌታ አንድ አንድ ሽንፈትና የአቻ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት ወልዋሎዎች ዳግም ወደ ስጋት ቀጠናው ተጠግተዋል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ክለቡ በዛሬው ዕለት ድል አድርጎ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻለ እስከ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አለው። ቡድኑ በታችኛው የደረጃ ሰንጠረዡ ክፍል ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ከቀጠናው ለመውጣት በሚደረገው ፉክክር የተሻለ ዕድል ለመያዝም በቀለሉ የማይጋለጥ የተከላካይ ክፍል ካለው የዛሬው ተጋጣሚው የሚጠብቀው ፈተና በድል መወጣት ይኖርበታል።
በአርባ አምስት ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ለመቅረብ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናል።
ከብዙዎች ግምት ውጭ ድንቅ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የሚገኙት ኤሌክትሪኮች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥብ አንዱን ብቻ ካሳኩባቸው መጥፎ ሳምንታት በኋላ ፋሲል ከነማን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰዋል። መሪው ሲዳማ ቡና በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ሳይጠበቅ ክፍት ወደ ሆነው የዋንጫ ፉክክር ለመቅረብ ዛሬ ሙሉ ነጥብ ማሳካት የሚጠበቅበት ቡድኑ ወደ ወሳኙ መርሐ ግብር በተሻለ ቁመና መቅረብ ይኖርበታል። በተለይም ሁለት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት ባስመዘገቡባቸው መርሐ ግብሮች ላይ አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ሦስት ጎሎች ማስቆጠር የቻለው የፊት መስመሩ ውጤታማነቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ 1 ጊዜ ድል ሲቀናው 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ወልዋሎ 5 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 3 ግቦች ማስቆጠር ችሏል።
ወልዋሎዎች አምበላቸው ፍሬው ሰለሞን እና አማካዩ ሙሉዓለም መስፍን ከቅጣት መልስ ያገኛሉ። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ቅጣት ላይ የነበረው ሀሰን ሑሴን ጨምሮ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሀዋሳ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
በአርባ አራት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ አርባ ምንጭ ከተማን ይገጥማሉ።
በሁለተኛው ዙር ባደረጓቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ድል ብቻ ማስመዝገብ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው መንፈቅ ባስመዘገቧቸው ደካማ ውጤቶች ከዋንጫ ፉክክሩ ለመራቅ ተገደዋል። የመጀመሪያውን ዙር ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ተመሳሳይ 35 ነጥብ ሰብስበው በግብ ክፍያ በ2ኛ ደረጃነት ያጠናቀቁት ሐይቆቹ የነበራቸው የመከላከልና የማጥቃት ጥንካሬ ማስቀጠል ባለመቻላቸው በሁለተኛው ዙር በእጅጉ ተዳክመዋል። በመጨረሻው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገምና ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ በሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታም ባለፉት ስድስት መርሐ ግብሮች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘት የቻለው ከፊት መስመራቸው ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

በሀያ ስምንት ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት አርባ ምንጭ ከተማዎች ድል አድርገው ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድላቸውን ለማለምለም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታሉ።
በመጨረሻው መርሐ ግብር በወላይታ ድቻ ተረተው ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት የቀመሱት አርባ ምንጭ ከተማዎች የውድድር ዓመቱ ጉዟቸው የሚያቃኑበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል። ሰባት ጨዋታዎች ብቻ በሚቀሩት ውድድር ዓመት በሊጉ ለመትረፍ ከባድ ፍልሚያ ማድረግ የሚጠበቅባቸው አዞዎቹ በቀሪዎቹ መርሐ ግብሮች በብዙ ረገድ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከተከታታት ሽንፈቶች መራቁ እንዲሁም ከላዩ ከተቀመጡ ክለቦች ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነት ማጥበብ መቻሉ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ያስመዘገባቸው ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ከግርጌው ፈቀቅ እንዳይል አድርጎታል። ከአንድ ጨዋታ በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታም ባለፉት ሁለት መርሐ ግብሮች አራት ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው የፊት መስመራቸው ውጤታማነት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
አርባምንጭ ከተማ ይገዙ ቦጋለን በጉዳት ምክንያት የሚያጣ እንደሆነ ተጠቁሟል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በረከት ሳሙኤልን በቅጣት ዛሬ አያገኝም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 21 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ 9 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ 5 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 36 ግቦች 20ዎቹ የሀዋሳ፤ 16ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።
ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ
በአርባ ሦስት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ ከሚያልመው አዳማ ከተማ ጋር ይጫወታሉ።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉትና በመርሐ ግብሮቹ ሦስት ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ በደካማ ወቅታዊ አቋም የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ደረጃቸው አሽቆልቁሏል። በባህርዳር ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተከታታይ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ዐፄዎቹ በደረጃ ሰንጠርዡ አካፋይ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ነጥብ ጥለው አጣብቂኝ ውስጥ ላለ መግባት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ካለ ወትሮው የተዳከመውና ባለፉበጨዋታዎችት አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስተናገደውን የተከላካይ ክፍላቸው እና አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመራቸው ድክመት ማረም ግድ ይላቸዋል።
በሰላሣ ስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ሦስት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ የሚረዳቸውን ድል ለማግኘት ፋሲል ከነማን ይገጥማሉ።
ከአስር ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሽረ ምድረ ገነትን አራት ለባዶ በመርታት ወደ አሸናፊነት የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ወሳኝ ሙሉ ነጥብ በመድገም ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። በወራጅ ቀጠናው ጫፍ 17ኛ ደረጃ ላይ ከተመቀጠው ሽረ ምድረ ገነት በሁለት ነጥብ ርቀት ብቻ የሚገኙት አዳማዎች ከወዲሁ ላለመውረድ ከሚደረገው ፉክክር ፈቀቅ ለማለት በመጨረሻው ጨዋታ በቡድኑ ላይ የታየው መነቃቃት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል። በተለይም በዕለቱ በአምስት መርሐ ግብሮች ካስቆጠራቸው ድምር ግቦች የላቀ በአንድ ጨዋታ ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው ብቃት ማስቀጠል ቀዳሚ የቤት ስራቸው መሆን ይገባዋል።
ፋሲል ከነማዎች በረከት ግዛውን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት እንዲሁም አምሳሉ ጥላሁንን በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አያገኙም።
ቡድኖቹ በሊጉ 18 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ በግንኙነታቸውም ያለፉትን አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ጨምሮ 11 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 5 ጊዜ ፋሲል 2 ጊዜ ደግሞ አዳማ አሸንፏል። ዐፄዎቹ 19 ግቦችን ሲያስቆጥሩ አዳማዎች ደግሞ 12 አግብተዋል።

