የቅድመ ጨዋታ መረጃ | የ36ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የቅድመ ጨዋታ መረጃ | የ36ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ36ኛው ሳምንት በሊጉ ለመቆየት በሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ ይቀጥላል። ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ

48 ነጥቦች ሰብስቦ አሁንም በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር እየተፎካከር የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ደረጃውን ይበልጥ ለማሻሻል ይጫወታል። ሀዋሳ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥብ 5 ብቻ ማሳካት የቻለ በመሆኑ ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ እንዳልሆነ ማሳያ ነው። ቡድኑ በነዚህ ጨዋታዎች ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 ቢያሸንፍም በሶስት ጨዋታዎች ላይ በጠባብ 1ለ0 እና 2ለ1 ውጤቶች ተሸንፎ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ግን በተከላካይ መስመር ላይ የሚታዩትን የትኩረት ማጣት ክፍተቶች ማረም እና የተጋጣሚን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች መዝጋት ይኖርበታል። በተለይም በሽግግር ወቅት ፈጣን መሆንና የፊት መስመር አጥቂዎቹ የሚያገኟቸውን ንጹህ የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር ይጠበቅበታል።

46 ነጥቦችን በመሰብሰብ 12 ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶች ደግሞ የደረጃ ሰንጠረዡን የነጥብ ፉክክር ለማጥበብ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ። ባህርዳር ካለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው 9 ነጥብ ሲሆን የቅርብ ጊዜ ጉዞው በአቻ ውጤቶች የተሞላ ነበር። ቡድኑ ፋሲል ከነማንና ድሬዳዋን በተመሳሳይ 2ለ0 ማሸነፍ ቢችልም ከመቐለ 70 እንደርታ፣ መቻል እና ወልዋሎ ዓዲግራት ጋር ነጥብ ተጋርቶ ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ዲቻ 2ለ0 የሆነ ሽንፈት አስተናግዷል። ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ በድል ለመወጣት በዋናነት ባለፈው ሳምንት በዲቻ ላይ የታየውን የመከላከል መዘናጋት በፍጥነት ማረም ይኖርበታል። በተጨማሪም በመሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ እና ፈጣን መስመር ሽግግሮችን በመጠቀም የፊት መስመር አጥቂዎቹን ማገዝ እንዲሁም የተገኙትን የግብ ዕድሎች ሳይባክኑ ወደግብነት መቀየር ይኖርባቸዋል።

ቡድኖቹ ከዚህ በፊት በሊጉ ደረጃ 14 ጊዜ ተገናኝተው ሐይቆቹ በአምስት ጨዋታ ድል ሲያደርጉ የጣና ሞገዶች አራት ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው 26 ግቦ ሲቆጠሩ ሀዋሳ 13 ግብ ባህርዳር ከተማዎች 11  አስቆጥረዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ያሬድ ብሩክ ከቅጣት ሲመለስ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። መሳይ አገኘው እና አማኑኤ ገብረሚካኤል ደግሞ በጉዳት ምክንያት ባህር ዳርን ዛሬ አያገለግሉም።

መቐለ 70 እንደርታ ከ አዳማ ከተማ

ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስቶች በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም ዛሬ ከአዳማ ከተማ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። በሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት ላይ ከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ በመግባቱ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሸገር ከተማን 1ለ0 ብቻ ሲሆን በሁለቱ ተሸንፎ በቅርብ ሳምንታት ደግሞ በተከታታይ ከባህር ዳር ከተማ እና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቶ ወሳኝ ነጥቦችን ጥሏል። የሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች እጅግ ጥቂት መሆናቸው ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ ይበልጥ አስጨናቂ አድርጎታል። ቡድኑ ዛሬ 3 ነጥብ ይዞ ለመውጣት ባለፉት ጨዋታዎች የታየበትን የግብ ማግባት ድክመት በአስቸኳይ ማረም እና የፊት መስመሩን በማጠናከር ግቦችን ማስቆጠር ይኖርበታል።

42 ነጥብ ይዞ በ15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ከስጋት ለመራቅ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙትን ምዕም አናብስቶችን ይገጥማሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ጠንካራውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ ነጥብ አሳክቶ የስነልቦና ጥንካሬን የፈጠረለት ቡድኑ ከታች ካሉ ክለቦች ስጋት ሙሉ በሙሉ ለመውጣት አሁንም ተጨማሪ ነጥቦች ያስፈልጉታል። ​ዛሬ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘውና በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል ከሚያደርገው መቐለ 70 እንደርታ ጋር የሚገጥም ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ካሉበት የደረጃ ስጋት አንጻር ጨዋታው እጅግ እልህ አስጨራሽና ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል። ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ በድል ለመወጣት የተጋጣሚውን ከፍተኛ ጫና መቋቋም የኋላ መስመር ጥንካሬውን ማስጠበቅ እና ባለፈው ሳምንት የታየውን የፊት መስመር ውጤታማነት ዛሬም በመድገም የግብ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅበታል።

ከዚህ በፊት በሊጉ 8ጊዜ ተገናኝተው መቐለ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲሆን አዳማ አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ ሲችል ሶስቱ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 15 ግቦች ሲቆጠሩ መቐለ 10  አዳማ ደግሞ 5 ግቦችን አስቆጥሯል።

መቻል ከ ኢትዮጵያ መድን

በደረጃ ሰንጠረዡ በ53 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መቻሎች ነጥባቸውን ለማሻሻል መድንን ይገጣማሉ። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲን 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ቢያሸንፍም ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ግን በአንድ አቻ እና በሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ነጥቦችን በመጣል ከዋንጫ ፉክክር ውጪ መሆኑ ይታወሳል። የቡድኑ ትልቁ ጥንካሬ በ35 ጨዋታዎች 43 ግቦችን ያስቆጠረውና በሊጉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው አስፈሪው የፊት መስመሩ ሲሆን የተከላካይ መስመሩም ያንያህል የሚታማ አይደለም ፤ ነገር ግን ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ የታየውን የመከላከል መዘናጋት ማስተካከል እና በመስመር የሚነሱ ጥቃቶችን በፍጥነት መዝጋት የሚጠበቅበት ቡድኑ ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የሆነውን የፊት መስመር ማጥቃት ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል።

በ46 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መድኖች ደረጃቸውን ለማሻሻል መቻልን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች 11 ነጥብ  ያሳካው ቡድኑ እጅግ አስደናቂና በጥሩ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው። የነጥብ ልዩነቱን ይበልጥ ለማጥበብና የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ከፍ ለማለት ከዛሬው ጨዋታ ጭምር ወሳኝ የሆነበት ቡድኑ የጀመሪያውን የሊግ ጉዞ ለማስቀጠል አሁን ያለውን ጠንካራ የኋላ መስመር ጥምረት ይዞ መቀጠልና በተለይም በመሀል ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ የኳስ ሽግግሮችን በማሳመር የፊት መስመር አጥቂዎቹን ማገዝ ይኖርበታል። እንዲሁም በጨዋታዎች ላይ የሚገኙትን ጥቂት የግብ ዕድሎች ሳይባክኑ ማስቆጠር ከቻለ የሊጉን ማጠቃለያ ሳምንታት በከፍተኛ የደረጃ ማሻሻል ማጠናቀቅ ይችላል።

በሊጉ 11 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ መቻል 5 ሲያሸንፍ መድን 4 ቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። 16 ግቦችን መረብ ላይ ሲያርፉ ሁለቱም ቡድኖች ስምንት ስምንት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

በመቻል በኩል የግብ ዘቡ አሊዮንዚ ናፊያን እና አጥቂው ኮሊንስ ኮፊ በጉዳት ምክንያት ዛሬ አይኖሩም። በመድን በኩል ደግሞ በረከት ካሌብ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

ሽረ ምድረገነት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሽረዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ይገጥማሉ። ካለፉት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው ጥቂት ነጥቦችን የሆነው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከሀዲያ ሆሳዕና እና ከነጌሌ አርሲ ጋር አቻ ቢለያይም ባለፈው ሳምንት በአርባምንጭ 2ለ0 መሸነፉ የወራጅ ቀጠና ስጋቱን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል። የቡድኑ ትልቁ ድክመትና ስጋት በ35 ጨዋታዎች ያስቆጠረው 21 ግብ ብቻ መሆኑ ሲሆን ይህ የፊት መስመር ብዙ ግብ አለማስቆጠር በሊጉ የመቆየት ተስፋውን አደጋ ላይ ጥሎታል። ቡድኑ ካለበት የወራጅ ቀጠና ስጋት አንጻር ዛሬ ነጥብ መጣል የማይታሰብ በመሆኑ ጨዋታው የሞት ሽረት ፍልሚያ ሆኖበታል። የዛሬውን ፈተና አልፎ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ባለፈው ሳምንት የታየውን የኋላ መስመር መላላት በአስቸኳይ ማረም እና የቅዱስ ጊዮርጊስን አስፈሪ ማጥቃት በጥንቃቄ መዝጋት ይኖርበታል።

በ49 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ የጀመሩትን ድንቅ የድል ጉዞ ለማስቀጠልና የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ይበልጥ ለመቅረብ ዛሬ በወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ የሚገኘውን ሽረን ይገጥማሉ። ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ድል ቀንቶት በአንዱ ብቻ አቻ በመለያየት በከፍተኛ ማሸነፍ ጉዞ እና አስፈሪ አቋም ላይ የሚገኘው ቡድኑ በተለይም ባለፈው ሳምንት ጠንካራውን መቻልን 3ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈበት መንገድ የቡድኑን ፍፁም የበላይነት ያሳየ ነበር። የፈረሰኞቹ ትልቁ ጥንካሬ በማጥቃት መስመራቸው ላይ ያለው ፍጥነትና በጨዋታዎች ላይ ወሳኝ ግቦችን አስቆጥሮ ውጤትን የማስጠበቅ ብቃታቸው ሲሆን ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ በወቅታዊነት ያለውን የተደራጀ የማጥቃት ጥንካሬ ይዞ መግባት እና በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል የሚያደርገውን የተጋጣሚውን እንቅስቃሴ ተጠቅሞ ቀድሞ ግብ ማግኘት ይጠበቅበታል።

ቡድኖቹ ከዚህ በፊት በሊጉ 6 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ፈረሰኞቹ በሶስቱ ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆን ቀሪዎቹ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። 6 ግቦችም የተቆጠሩ ሲሆን ስድስቱንም ቅዱስ ጊዮርጊስ የሽረ መረብ ላይ አሳርፏል።