ወላይታ ድቻን ከነበረበት የወራጅ ስጋት ያላቀቁትን አሰልጣኝ በቡድኑ ለማቆየት መቃረባቸውን አውቀናል።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማሯቸው ያላማረላቸው ወላይታ ዲቻዎች በከፍተኛ የመውረድ ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበረ አይዘነጋም። የጦና ንቦቹ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ወደ ኃላፊነት ካመጡ ወዲህ ቡድኑ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቶ በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጥ ከመቻሉ ባሻገር በደረጃ ሰንጠረዡ ሃምሳ አንድ ነጥብ በመያዝ ሰባተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ዛሬ የክለቡ ያለፉት ሂደቶች እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባሮች ዙርያ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን በዋናነት ቡድኑ በውጤት ቀውስ ውስጥ በሚገኝበት ሰዓት ተረክበው የተሻለ ውጤት ያመጡትን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ወደ ክለቡ መቀመጫ ወላይታ ሶዶ በመጥራት ከጦና ንቦቹ ጋር አብረው እንዲቀጥሉ እና ውላቸውን ለማደስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ ድርድሮችን አድርገዋል። ድርድሩም በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን እና አሰልጣኝ መሳይ ከወላይታ ድቻ ጋር ለሁለት ዓመት አብረው ለመቆየት መስማማታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

