ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ በአውሮፓ ትገኛለች

ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ በአውሮፓ ትገኛለች

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አጥቂ በአውሮፓው ክለብ እንደምትገኝ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የአራት ዓመት ምሩቅ ናት በእግርኳስ ህይወቷ ላይ በምታሳየው ከፍተኛ ዕድገት በፍጥነት ነበር እራሷን ለስፖርት ቤተሰቡ ማስተዋወቅ የጀመረችው። በኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሁሉም የዕድሜ ዕርከን ተጫውታ ያሳለፈችው የመስመር አጥቂዋ ንግስት በቀለ በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓዊቷ ሀገር ፈረንሳይ የምትገኝ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ የሙከራ ዕድል አግኝታ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በመቻል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውታ ያሰለፈችው ተስፈኛዋ ወጣት የሙከራ ዕድል የሰጣት በፈረንሳይ የሚገኝ ክለብ እንደሆነ ብናቅም የክለቡን ስም ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ንግስት ወደ ስፍራው ካቀናች ስምንተኛ ቀን ሲሆናት እስካሁን ባለው ሂደት በጥሩ የሙከራ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ዙርያ አዳዲስ ተጨማሪ መረጃ ይዛ የምትመለስ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።