ትልቅ ተስፋ የተጠለበት ትውልደ ኢትዮጵያዊ በቡንደስሊጋው ክለብ ውሉን አራዘመ

በአሰልጣኝ ክርስቲያን ኢልዘር በሚሰለጥነው ሆፈንሃይም ዋናው ቡድን ተካቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናትናኤል አብርሀ ከቡድኑ ጋር ለመቀጠል የረዥም ጊዜ ውል ተፈራርሟል። የ18 ዓመቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ባለፈው የውድድር ዓመት በጀርመን ሦስተኛ የሊግ እርከን ተሳታፊ በሆነው ሆፈንሃይም II ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ከዋናው ቡድኑ ጋር ለማሳለፍ ውሉን ማራዘም ችሏል።
የኢንትራክት ፍራንክፈር የወጣት ቡድኖች ውጤት የሆነው እና ከዓመታት በፊት አሳዳጊ ክለቡን በመልቀቅ ሆፈንሃይምን የተቀላቀለው ተጫዋቹ ወደ ዋናው ቡድን ከማደጉ በፊት ኮሎኝን በማሸነፍ የጀርመንን ከ19 ዓመት በታች ቻምፕዮና በሆነው ስብስብ ውስጥ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ክስተት ተጫዋች እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ከክለብ እግር ኳስ በተጨማሪ በጀርመን ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች መጫወት የቻለው ተጫዋቹ ከስነ ስርዓቱ በኋላ ከክለቡ የሚድያ ክፍል ባደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ደስታውን ገልጿል። “ወደ ሆፈንሃይም ከ19 ዓመት በታች ለመዘዋወር መወሰኔ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር። አሰልጣኞቹ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እንድሻሻል ረድተውኛል ፤ አሁን ከዋናው ቡድን ጋር ሆኜ በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ጨዋታዬ ማድረግ እፈልጋለሁ ” ብሏል

