መቻል ስፖርት ክለብ ዓመታዊ የማጠቃለያ መርሐግብሩን በደማቅ ሁኔታ ሲያከናውን ከጎፈሬ ጋር ያለውን ውልም ለተጨማሪ ዓመታት አራዝሟል።

ዛሬ በመኮንኖች ክበብ እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ በተካሄደው መርሐግብር የመከላከያ የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ ፣ የመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን ፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር መክዩ መሐመድ ፣ ባለሃብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ፣ የጎፈሬ መሥራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና በተለያየ ዘርፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞች እና አሰልጣኞች የተገኙ ሲሆን መቻል ስፖርት ክለብ ዓመታዊ የማጠቃለያ መርሐግብሩን አከናውኖ ስፖርተኞችን ሲሸልም ከጎፈሬ ጋር ያለውን ውልም ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አራዝሟል።

መቻል ስፖርት ክለብ በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥ ውድድሮች በመሳተፍ 35 የወርቅ ሜዳሊያ ፣ 32 የብር ሜዳሊያ እና 51 የነሃስ ሜዳሊያ በአጠቃላይ 118 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ጥንካሬውን እያስቀጠለ ይገኛል።
በተጨማሪም 16 ሪከርዶችን በማሻሻል 7 ዋንጫዎችን ማግኘት የቻለ ሲሆን 9 ተወዳዳሪዎች እና 2 አሰልጣኞች ሀገራቸውን ወክለው በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ መሆኑን እና በዚህም የወርቅ ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው ማምጣታቸው ተገልጿል።

በግሪክ በተካሄደው በ60ኛው የዓለም የወታደራዊ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ በዱላ ቅብብል ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የተቋሙን እና የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ክፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ መቻላቸው ታውቋል።
መቻል ከስፖርት ትጥቅ አምራቹ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጋር ላለፉት ሦስት ዓመታት የፈጸመው ውል እጅግ ስኬታማ እንደሆነ ጠቅሶ በሀገር ውስጥ ምርት ፈር ቀዳጅ በመሆኑም አድናቆቱን በመግለጽ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም አብሮ ለመሥራት ውል ተፈራርሟል። በዚህም የጎፈሬ ስፖርት ትጥቅ ብራንድ መሥራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እና የመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን ውሉን በሰነድ ተፈራርመዋል።

በመጨረሻም የክብር እንግዶች ውጤት ላስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ፣ አሰልጣኞች ፣ ባለሙያዎች የማዕረግ እና የገንዘብ ሽልማቶችን ካበረከቱ በኋላ ተቋሙ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ እንዲቀርብ አሳስበው መርሐግብሩ ተጠናቋል።

