የ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቡድናቸውን ማጠናከራቸውን በመቀጠል ሁለት ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ኮከቦችን በይፋ አስፈርመዋል።

ምህረት አየለ ሀምራዊ ለባሾቹን ተቀላቅላለች። ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተገኝታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ዘንድሮ ድንቅ ጊዜ ያሳለፈችው ባለክህሎቷ አጥቂ በተለይም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እስከመጨረሻው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላደረገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና የተወጣች ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለብርሃኑ ግዛው ቡድን ለመጫወት በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽን በመገኘት ፈርማለች።
ሊዲያ እያሱ ሌላዋ ባንክን የተላቀለች ተጫዋች ናት። በጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ድንቅ ጊዜያት ያሳለፈችው ሊዲያ ዘንድሮ የኢትዮፕያ ሴቶች ከፍተና ጎል አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን ከ17 እና ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ላይም ጎልታ መውጣት ችላለች። ሊዲያ በባንክ የሁለት ዓመት ውል ተፈራርማለች።
በሴካፋ ዞን ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ላይ የሚሳተፈው ንግድ ባንክ ከዚህ ደቀም የምስራች ላቀው እና ገነት ኤርሚያስን ሲያስፈርም የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ማደሱ ይታወሳል።

