የግል አስተያየት | የዘገየ ውሳኔና የባከነ ዕድል ፤ ክፍል 2

የግል አስተያየት | የዘገየ ውሳኔና የባከነ ዕድል ፤ ክፍል 2

ክፍል ሁለት ፡ የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ልማት ስትራቴጂ

በኢዝ-አሻራ (የብዕር ስም)

ክፍል አንድ ፅሑፌ ስለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሴቶች እግርኳስ እቅድ የተሻለ ምስል እንዲኖረን የዓለም አቀፉን እግርኳስ ማህበር ፊፋን የእቅድ ዓላማ ጊዜና የእቅድ አተገባበር ደረጃዎችን ለማስቃኘት ሞክሬያለው፡፡ በተነሱት ዝርዝር የፖሊሲና ፕሮግራሞች እንዲሁም ስትራቴጂና ኢኒሼቲቮች አንፃር በዚህ ክፍል – የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን እቅድ ወቅቱን ባለመጠበቁ ከአለም አቀፉ ስትራቴጂ እቅድ ቀሪ ግዜ አንፃር ይሳካ ይሆን? ምን ተስፋ አለው? ፈተናዎቹስ? ያጣናቸው እድሎችስ ? ሌሎች ሀገራት በተለይ ጎረቤት የምስራቅና የመካከለኛ አፍሪካ አገራት በዚህ ስትራቴጂ ምን ተጠቀሙ እንዴት? የሚሉትን እንዳስሳለን፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በፊፋ የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመተግበር የራሱን የሶስት ዓመት ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም የትግበራ ቆይታ የሚኖረው የሴቶች እግር ኳስን በታዳጊዎች ደረጃ መሠረት ከመጣል ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ቡድን ያለውን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ እቅድ ማዘጋጀቱን አሳውቋል። ሀገርን እንደሚወክል ትልቅ ተቋም ከዓመት በላይ እያቀደ መስራቱ በራሱ ጥሩ እርምጃ ቢሆንም እቅድ ዝግጅቱ ግን የሂደት መዘግየት፣ የጊዜ መባከንና የሀገር እድል ማሳጣት ጉዳዮች በሰፊው የሚያስነሳ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ፊፋ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ያስጀመረውን ይህንን ፕሮግራምና ስተራቴጂ እቅድ ኢትዮጵያ ከ7 ዓመት በኋላ የአለም አቀፉ እቅድ ሊጠናቀቅ 1 ዓመት ተኩል በቀረበበት ጊዜ ገና ለመጀመር ማወጇ ለምን ዘገየ ማነው ያዘገየው እንዴት ተብሎ ብዙ መጠየቅ ይቻል ይሆናል ትልቅ የሀገር ጉዳይ ነውና መጠየቅ ያለበት አካል እንዲጠይቅ እየተውኩ። ለዚህ ፅሁፍ ዓላማ ሲባል የምንማርበት ላይ ትኩረት በማድረግ በመዘግየቱ ያጣናቸውን እድሎችን እንዲሁም ስትራቴጂው አሁን ካለው ቀሪ ግዜ አንፃር ምን ተስፋ አለው የሚሉትን ላንሳ።

ማንኛውም ስትራቴጂ እቅድ በሰነድነቱ ብቻ አይለካም ፤ ይልቁን የሚለካው በተግባር በሚፈጥረው ውጤት ለውጥ በመሆኑ እቅዱ ቢያንስ ያለመውን በጀት ማስለቀቅ ችሎ (Financial Unlocking) በቀሪው ጊዜ ለሴቶች እግርኳስ ልማት የተመደበውን በጀት በቀጥታ ለማግኘት እና ለመጠቀም መንገድ ካስከፈተና እንደ ሌሎቹ ጎረቤት አባል አገራት ስኬት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ልማት ፕሮግራሞች ከተዘረጋ፣ የሴት አሰልጣኞች፣ ዳኞችና አስተዳዳሪዎች ቁጥር ከጨመር፣ ክለቦች ትርጉም ያለው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኙ ካደረገ እና ቢያንስ እንደነ ኬንያ ታንዛንያና ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪነቱን ካሻሻለ መልካም አፈፃፀም ሊባል ይችላል፡፡

ነገር ግን ከስትራቴጂው ዓላማዎች ይዘት ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ከሚፈልጉት ጊዜ አንፃር ሲታይ ቀዳሚው ጥያቄ የጊዜ እጥረት ነው ፊፋ በ10 ዓመት ያቀደውን መዋቅራዊ ለውጥ በ3 ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ መሞከር በወረቀት ላይ ከሚፃፍ እቅድ ያለፈ ውጤት አይኖረውም፡፤ ባለው ጊዜ እጅግ ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እናሳከለን የሚል ቁርጠኝነት ቢኖር እንኳን ለእቅዱ ውጤታማነት ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ የአስፈፃሚ አካላት አቅም ነው፡፡ይህ የብዙ አፍሪካ አገሮች እጅግ መሰረታዊ ድክመትና ፈተና እንደሆነ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከፌዴሬሽኑ ባሻገር በየ ክልል እግር ኳስ መዋቅሮች ውስጥ የሴቶች እግር ኳስን ብቻ የሚመለከት መዋቅር እንዲሁም በፕሮፌሽናል ደረጃ ራሱን የቻለና የሙሉ ጊዜ የአመራርና የባለሙያዎች እጥረት ባለበት ሁኔታ የእቅዱን አፈፃፀም ስኬት ጥያቄ ውስጥ ስለሚከተው ካጣነው እድል በላይ በቀሪ ጊዜ የእቅዱ አተገባበር ውጤታማነት እጅግ አሳሳቢ ነው።

የሌሎች አገራት ተሞክሮን መነሻ በማድረግ ያጣናቸውን እድሎች የስትራቴጂ መዘግየት የጊዜ ብቻ ኪሳራ ሳይሆን እንደ አንድ ቀደምት የአፍሪካ አገር አባል ቀደም ብለን ጀምረን ቢሆን ኖሮ ልናገኝ የሚገባንን ከፍተኛ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች መገመት ይቻላል ነገር ግን ሳንጠቀም በመቅረታችን ከፍተኛ እድል ያለመጠቀም ኪሳራ አጋጥሞናል። በወጣት ተጫዋቾች ላይ ሊፈጠር የነበረው ዘላቂ የልማት ሥርዓት አዘግይቷል። ዛሬ በብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብዙዎቹ ከ8 ወይም 10 ዓመታት በፊት በዕድሜ ታዳጊዎች ፕሮግራም ታቅፈው የቆዩ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። መዘግየቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነበራትን ታሪካዊ የእግር ኳስ ስም በሴቶች እግር ኳስም ለመገንባት ያለውን እድል አጥታለች።

የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ አገራትን ንፅፅር
በቅርብ ዓመታት ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ብሩንዲ የሴቶች እግር ኳስን በሀገራዊ ስትራቴጂያቸው ውስጥ በማካተት የሊግ ውድድሮችን፣ የወጣቶች ፕሮግራሞችን፣ የአሰልጣኝና የዳኝነት ሥልጠናዎችን አጠናክረዋል። በውጤቱም በCAF ውድድሮች ተሳትፎ፣ በFIFA የልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚነት፣ በሴት ተጫዋቾች ሙያዊ እድል እና በክለቦች አደረጃጀት ላይ በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለውጥ አምጥተዋል።እነዚህ ሀገራት የፊፋን የሴቶች እግር ኳስ ልማት በጀት እና የቴክኒክ ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀማቸው አህጉራዊ ውጤት ማምጣት ችለዋል፡፡ አነዚህ ሀገሮች በአሁን ወቅት በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በካፍ ሻምፕዮንስ ሊግ እያደረጉት ያለው ተሳትፎና ውጤት ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በህዝብ ብዛትና በተፈጥሮ ተሰጥኦ ከእነዚህ ሀገሮች የምትበልጥ ብትሆንም በአስተዳደር ፍጥነትና በስትራቴጂ አፈጻጸም ግን ከኋላ ቀርታለች። ይህ የሀብት እጥረት ሳይሆን የአስተዳደርና የመሪነት ክፍተት ነው። የኢትጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው የስትራቴጂ እቅድ ከዓለም አቀፍ አቅጣጫ በኋላ ብቻ የሚመጣ ከሆነ፣ ተቋሙ ራሱ ለውጥን የሚመራ ሳይሆን ለውጥን የሚከተል መሆኑን ያሳያል። ዘመናዊ መሪነት አስቀድሞ ያቅዳል፣ ራዕይ ያስቀምጣል፣ አቅም ይገነባል፣ ሀብት ያሰባስባል፣ ከለውጡ በፊት ለውጡን ያዘጋጃል።

መደምደሚያ

የሴቶች እግር ኳስ የልማት እቅድ መኖሩ የሚያስደስት ነው። ነገር ግን የሚያስፈልገው አዲስ ሰነድ ሳይሆን አዲስ የአስተዳደር ባህል ነው። እቅዶች በጊዜያቸው ሲዘጋጁ፣ በተጠያቂነት ሲተገበሩ እና በሚለካ ውጤት ሲገመገሙ ብቻ የሴቶች እግር ኳስ ከተስፋ ወደ ስኬት ይሸጋገራል። ዛሬ የሚነሳው ጥያቄ እቅዱ ተጻፈ ወይስ አልተጻፈም የሚል አይደለም፤ ይህ እቅድ የጠፋውን ጊዜ ይመልሳልን ? ወይስ ሌላ የዘገየ ተስፋ ብቻ ይሆናል ? የሚለው ነው።