ነፃነት ገብረመድህን ወደ ክለቡ ይመለሳል

ነፃነት ገብረመድህን ወደ ክለቡ ይመለሳል

ላለፉት ቀናት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ዝግጅት በማድረግ ላይ የቆየው ተከላካይ በክለቡ ጥያቄ መሰረት ይመለሳል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ላለበት ጨዋታዎች ጥሪ ካደረገላቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የመሀል ተከላካዩ ነፃነት ገብረመድህን ክለቡ ወልዋሎ በነሐሴ 13 በደብዳቤ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከነገ ነሐሴ 16 ጀምሮ ወደ አዳማ ከተማ ተጉዞ ወደ ክለቡ ወልዋሎ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንዲቀላቀል ፍቃድ ተሰጥቶታል።

ከሱዳኑ ሂላል አልሳሕል ጋር ላለባቸው የካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከአራት ቀናት በፊት በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ወልዋሎዎች ተከላካዩ የዝግጅቱ አካል እንዲሆን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በነገው ዕለት ቡድናቸውን የሚቀላቀል ሲሆን ፌደሬሽኑም ተጫዋቹ በሚፈለግበት ሰዓት ዳግም ጥሪ ሲደረግለት ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀል አሳውቋል።

በቅርብ ዓመታት ጥሩ ብቃት ካሳዩ ወጣት ተከላካዮች አንዱ የሆነው ነፃነት ገብረመድህን ከዚህ ቀደም በአሳዳጊ ክለቡ ሽረ ምድረ ገነት ጨምሮ በወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን ከብሔራዊ ቡድኑ የደረሰው ጥሪም የመጀመሪያው ነው።