የወልዋሎ ዓዲግራት ተጋጣሚ ማነው ?

የወልዋሎ ዓዲግራት ተጋጣሚ ማነው ?

በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወልዋሎ ዓ/ዩ የሚገጥመው ክለብ ማነው?

የኢትዮጵያ ዋንጫን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በታላቁ አህጉራዊ ውድድር ለመሳተፍ የበቃው ወልዋሎ ዓ/ዩ በአህጉራዊው መድረክ የመጀመርያ የማጣርያ ፍልሚያውን ለማድረግ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ አምርቷል። በነሐሴ 29 በሚደረገው የመጀመርያ ዙር ጨዋታ የሱዳኑን ሂላል አል-ሳሕል የሚገጥሙት ቢጫ ለባሾቹ ከተጋጣሚያቸው ጋር ለሚያደርጉት ብርቱ ፍልሚያ ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ አድርገዋል።

ሂላል አል-ሳሕል እግር ኳስ ክለብ ማነው ?

❖ በግሪጎርያን አቆጣጠር በ1937 ከሱዳን ዋና የባህር በር ከተሞች አንዷ በሆነችው ፖርት ሱዳን፤ ሂላል አል-ሳሕል በሚል ስያሜ የተቋቋመው እና “አል-ሳሕሊያ” በሚለው የቅጽል ስሙ የሚታወቀው ክለቡ በሀገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። እ.ኤ.አ በ1992 የሱዳን ፕሪምየር ሊግን በማሸነፍ ከዋና ከተማዋ ካርቱም ውጭ ዋንጫውን ወደ የባህር ዳርቻዋ ከተማ መውሰድ የቻለ ጥቂት ስኬታማ ቡድን ነው።

የአህጉራዊ ውድድር ስኬት ?

❖ ሂላል አል-ሳሕል በአህጉራዊ ውድድር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ተሳትፎ አለው። እ.ኤ.አ በ1993 በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ (በወቅቱ የአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮንሺፕ) ተሳትፎ የነበረው ሲሆን በ2022/23 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደግሞ እስከ ሁለተኛው የማጣሪያ ዙር ድረስ መጓዝ ችሏል።

የክለቡ አሰልጣኝ

❖ የሂላል አል-ሳሕል ዋና አሰልጣኝ ልምድ ያላቸው ሱዳናዊው አሰልጣኝ ናዲር ዛርግ አክላንድ ናቸው። ቡድናቸውን በተደራጀ የተከላካይ መስመር እና በፈጣን የመስመር ጥቃቶች (Counter-attacks) ላይ በተመሰረተ የታክቲክ ውቅር የሚያሰልፉት አሰልጣኙ በተለይም በአካላዊ ፍልሚያ ላይ የተደገፈ ጠንካራ ስብስብ ገንብተዋል።

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች?

❖ በቡድኑ ውስጥ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም ከሁሉም የላቀ አበርክቶ ያለው የ30 ዓመቱ የፊት መስመር አጥቂ ሙጃሂድ ፋሩቅ ግን የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው። በአየር ላይ ኳሶች ያለው የበላይነት እና በሳጥን ውስጥ ያለው የግብ ማስቆጠር ብቃት የቡድኑ ዋና የጥቃት መሳሪያ ያደርገዋል።

ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበት ቀን እና ስታዲየም ?

❖ የክለቡ ዋና ስቴድየም በፖርት ሱዳን የሚገኘው 13,000 ደጋፊዎች የመያዝ አቅም ያለው Port Sudan Stadium ነው። ሆኖም በሱዳን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ጨዋታውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ ተገዷል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ጨዋታ ዓርብ ነሐሴ 29 ቀን በሩዋንዳ ኪጋሊ በሚገኘው ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይከናወናል።

የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ቅዳሜ መስከረም 2 ቀን በኢትዮጵያ ድሬዳዋ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።