ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጋቦናውያን አጥቂ የግላቸው አድርገዋል

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጋቦናውያን አጥቂ የግላቸው አድርገዋል

የ2026 የጋቦን ኮከብ ተጫዋች መዳረሻው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የወቅቱን የጋቦን ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢ እና ምርጥ ተጫዋች ካሌብ ስቴፍ ሜልቪን ንዛምባን ለማስፈረም መስማማቱ ታውቋል። ይህ የ20 ዓመት ወጣት ጋቦናዊ አጥቂ ካሳለፈው አስደናቂ የውድድር ዘመን በኋላ በበርካታ ታላላቅ የሀገር ውስጥ ክለቦች ሲፈለግ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም የኤሌክትሪክን ማሊያ ለመልበስ ወስኗል። ንዛምባ በጠንካራ የግራ እግር ምቱ እና ሁለገብ ተጫዋችነቱ የሚታወቅ ሲሆን በዋና አጥቂነት፣ በቀኝ ክንፍ እና በአጥቂ አማካይነት መጫወት ይችላል።

ንዛምባ በጋቦኑ ቫውቱር ክለብ ደ ሊብሬቪል ባሳለፈው አስደናቂ የውድድር ዘመን በ24 ጨዋታዎች 13 ግቦችን በማስቆጠር እና 8 የግብ እድሎችን አመቻችቶ በማቅረብ የወቅቱን የ”Ndambo d’Or 2026″ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት አሽንፏል። በተጨማሪም በ7 ጨዋታዎች የኮከብ ተጫዋችነት ክብርን የተቀዳጀው ይህ አጥቂ ከኢትዮጵያ፣ ቱኒዚያ እና ግብፅ ታላላቅ ክለቦች ከፍተኛ የዝውውር ጥያቄ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ለመጫወት ወስኗል። የ1.86 ሜትር ቁመት ያለው ይህ ረጅም ተጫዋች የክለቡን የአጥቂ መስመር በእጅጉ እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።