በቅርቡ ዋልያዎቹን የሚገጥመው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ጓንቱን ሰቀለ

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹን የሚገጥመው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ለረዥም ዓመታት ያገለገለውን ስኬታማ ግብ ጠባቂው አጥቷል። ከቡድኑ ራሱን ያገለለውም ኤድዋርድ ሜንዲ ሲሆን ከቴራንጋ አናብስት ጋር ከነበረው አስደናቂ የስኬት ዓመታት በኋላ ጓንቱን መስቀሉ ተከትሎ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከሚገጥመው ስብስብ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።
ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ካሳካቸው ስኬቶች ባሻገር በአውሮፓም አስደናቂ የክለብ እግር ኳስ ህይወት የነበረው ግብ ጠባቂው ከቼልሲ ጋር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማሳካቱ የሚታወስ ሲሆን ሀገሩ ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ የአህጉሪቱን ዋንጫ ባሳካችበት የ2021 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ምርጥ ብቃቱ ማሳየቱ ይታወሳል። በቅርቡ የቀድሞ የአርሰናል አማካይ ፓትሪክ ቬራን በአሰልጣኝነት የቀጠረችው ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታ በመስከረም አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደምትገጥም ይታወቃል።

