አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከሲዳማ ቡና የመረጧቸው ተጫዋቾች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ሲያደርጉ የአንድ ተጫዋቾች ስም ግን አለመካተቱ ታውቋል።

ከሱዳን እና ሴኔጋል ጋር ለሚደረጉት ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች ዝግጅቱን አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ላይ እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና 6 (መጀመሪያ 7 ነበር ፤ ወዲያው ታዳጊው ግብ ጠባቂ ትንሳኤ ማርቆስ መቀነሱ ልብ ይሏል) ተጫዋቾችን መርጦ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾቹ በነበረባቸው አህጉራዊ ግዳጅ ቡድኑን ሳይቀላቀሉ ቀርተው ነበር። ታዲያ ዛሬ ቡድኑ የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካጠናቀቀ በኋላ ጥሪ የደረሰላቸው ተጫዋቾች ከነገ በስትያ ማክሰኞ ዋልያዎቹን እንዲቀላቀሉ መልዕክት ተላልፏል።
ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ግን የመስመር ተከላካዩ ደግፌ ዓለሙ ከስብስቡ መቀነሱ ታውቋል። ተጫዋቹ በምን ምክንያት እንደተቀነሰ በግልፅ ባይታወቅም ከእርሱ ውጪ ያሉት የቡድኑ ተጫዋቾች ማለትም አቤል ያለው፣ ያሬድ ባዬ ፣ ብርሃኑ በቀለ፣ መስፍን ታፈሰ እና ቢንያም በላይ ማክሰኞ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ተመላክቷል።

