የፊታችን ማክሰኞ ከዋልያዎቹ ጋር የሚፋለሙት የቴራንጋ አንበሶቹ እጅግ በርካታ የልዑካን ቡድን በመያዝ ወደ ሀገራችን እየመጡ ነው።

በቀጣዩ የአህጉሪቱ የብሔራዊ ቡድኖች ትልቁ የውድድር መድረክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ፍልሚያዎች እየተከናወኑ ሲሆን በምድብ አስር ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ሞዛምቢክ ጋር የተደለደለውና የፊታችን ማክሰኞ በውቡ የባህርዳር ስታዲየም የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ዓርብ ማፑቶ ላይ ከሞዛምቢክ ጋር ጨዋታውን ካከናወነ በኋላ እዛው የአንድ ቀን የልምምድ መርሐግብሩን አከናውኖ ከደቂቃዎች በፊት ሁለተኛ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ኢትዮጵያ ጉዞውን ጀምሯል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በቻርተር አውሮፕላን ከሞዛምቢክ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ የሚገኝ ሲሆን ከስድስት ሰዓታት የዐየር ላይ ቆይታ በኋላ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ ገብቶ ወዲያው ወደ ባህር ዳር በማቅናት ምሽት ላይ ባህር ዳር የሚገባ ይሆናል።
በሴኔጋል በኩል ከ70 በላይ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ እንደሆነ የሰማን ሲሆን ቡድኑም ዛሬ ምሽት ባህር ዳር ከገባ በኋላ ነገ በባህር ዳር ስታዲየም ብቸኛ የኢትዮጵያ ላይ ልምምዱን አከናውኖ ለማክሰኞው ጨዋታ እንደሚዘጋጅ ታውቋል።
የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር በሚኖረው ቆይታ በተለምዶ አባይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ባለአራት ኮከቡ ናይል ቪው ሆቴል ማረፊያውን እንደሚያደርግ አውቀናል።

