የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የትናንትናው የልምምድ መርሐግብር ምን ይመስል ነበር?

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የትናንትናው የልምምድ መርሐግብር ምን ይመስል ነበር?

ዓርብ ከሞዛምቢክ ጋር 1ለ1 የተለያየውና የፊታችን ማክሰኞ ዋልያዎቹን የሚገጥመው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ትናንት የሰራው ልምምድ ምን ይመስላል?

ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በሚያስተናግዱት የ2027 የአህጉሪቱ ትልቁ የውድድር መድረክ ለመሳተፍ 48 ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን ካሳለፍነው ሀሙስ አንስቶ ማድረግ ጀምረዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሱዳን እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድላ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዓርብ አከናውና 1ለ0 የተሸነፈች ሲሆን ሁለተኛ ጨዋታዋን ደግሞ በሜዳዋ እና በደጋፊዋ ፊት ማክሰኞ ከሴኔጋል ጋር ታከናውናለች። ተጋጣሚያችን ሴኔጋልም ማፑቶ ላይ ድል ያልቀናት ሲሆን ከብዙዎች ግምት በተቃራኒ ከአንድ ነጥብ በላይ ከጨዋታው ማግኘት አልቻለችም።

ታዲያ ማክሰኞ ባህር ዳር ላይ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ አስፈላጊ ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን ቡድኖቹም ከዓርቡ የውጤት ድባቴ በመውጣት ትኩረታቸውን የማክሰኞ ጨዋታ ላይ አድርገው እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ትናንት አመሻሽ ባህር ዳር የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዓርቡ ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ከሰዓት የመጀመሪያ ልምምዱን የሚሰራ ሲሆን ሴኔጋሎች በተቃራኒው እዛው ሞዛምቢክ ማቶላ ላይ በላልጊ አሬና ልምምዳቸውን ትናንት አከናውነዋል።

የቴራንጋ አንበሶቹ በእውቁ የቀድሞ የእግርኳስ ተጫዋችና የአሁኑ አሠልጣኝ ፓትሪክ ቪየራ እየተመሩ ብዙዎች ከጠበቁት በታች ውጤት ካስመዘገቡበት የዓርቡ ጨዋታ ማግስት አመሻሽ ላይ በሰሩት ልምምድ በሞዛምቢኩ ጨዋታ ምንም ደቂቃ ያላገኙና ትንሽ ደቂቃ ብቻ በጨዋታው ተቀይረው በመግባት ተሳትፎ ያደረጉ ተጫዋቾችን ተሳትፈው ልምምድ ሰርተዋል። በዓርቡ ጨዋታ በቋሚነት የተሳተፉ ተጫዋቾች ግን ልምምድ ሳይወጡ እዛው ሆቴላቸው እረፍት እንዲያደርጉ ተደርጓል።

ከስፍራው እንደወጡ መረጃዎች ከሆነ የልምምድ መርሐ ግብሩ ላይ በዓርቡ ጨዋታ ላይ ያልነበሩ ተጫዋቾች የጨዋታ ዝግጁነታቸው ከፍ እንዲል ከፍተኛ አካላዊ ጥንካሬን የሚጠይቁ ሩጫዎች እንዲሁም የአካል ብቃት ላይ ያተኮሩ ልምምዶች እንደተሰጡ ተጠቅሷል። በተጨማሪም በአነስተኛ ሜዳ የቡድን ጨዋታ ተደርጎ የቅንጅት ስራዎች እንደተሰሩ ተመላክቷል።

ከልምምዱ ጋር በተያያዘ ዜና የሁለት ጨዋታዎች እገዳ በካፍ የተጣለበት ኢሊማን ንዲዬ በትናንትናው የልምምድ መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፏል። የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች ኢሊማን ንዲዬ ሀሙስ የቪየራን ስብስብ ከተቀላቀለ በኋላ በትናንትናው የልምምድ መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሳተፍ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጉም ተገልጿል። በልምምዱ ላይ በተከናወነው የአጭር ሜዳ የ8 ተጫዋቾች ጨዋታ ላይም እርሱ የሚሳተፍበት ቡድን አሸንፏል። ተጫዋቹ የስብስቡ አካል ቢሆንም ቅጣቱን ስላልጨረሰ በማክሰኞ የኢትዮጵያ ጨዋታ ግን አይሰለፍም።