“ሦስቱን ነጥቦች ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ እንጓዛለን” ካሊዱ ኩሊባሊ
የሴኔጋሉ ኮከብ ካሊዱ ኩሊባሊ ቡድናቸው የትናንትናውን የልምምድ መርሐ ግብር ካጠናቀቀ በኋላ ስለቡድናቸው እና ስለዋልያዎቹ ጨዋታ አስተያየት ሰጥቷል።

በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር የተደለደለች ሲሆን ባሳለፍነው ዓርብም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን አድርጋ በሱዳን አንድ ለምንም ተሸንፋለች። የፊታችን ማክሰኞ የዋልያዎቹ ተጋጣሚ የሆነው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከሞዛምቢክ ጋር 1ለ1 ተለያይቷል። ታዲያ ለሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች አስፈላጊ ከሆነው የማክሰኞ ጨዋታ በፊት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ካሊዱ ኩሊባሊ ትናንት ቡድኑ ልምምዱን ከሰራ በኋላ ተከታዩ ቆይታ መገናኛ ብዙሀን ጋር አድርጓል።
ስለሰሩት ልምምድ
”ጥሩ የልምምድ ክፍለ ጊዜ ነበር። ትላንት በቋሚነት በተሰለፉት ተጫዋቾች ላይ የታየውን አካላዊ ድካም ለማካካስ የታለመ የጥንካሬ ልምምድ ነበረው። ስለዚህ ጥሩ ልምምድ ነበር ፤ በጥሩ ሁኔታ ሰርተናል ፤ በደንብም ሮጠናል። ከዚያ ውጭ ደግሞ አዝናኝና የውድድር ስሜት ያለው ልምምድም ሰርተናል።”
ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው ቀጣይ ጨዋታ ስለሰጡት ትኩረት
”አዎ! በቀጣዩ ጨዋታ ላይ ትኩረት አድርገናል። ከሞዛምቢክ ጋር ያደረግነውን የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልግ ነበር። ማሸነፍ ባንችልም በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳየነው የጨዋታ ይዘት ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ችለናል። ከዚህ አስቸጋሪ ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል ፤ ይህም ጥሩ ነው። አሁን ደግሞ ሶስቱን ነጥቦች ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ እንጓዛለን። ለአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያና ወደፊት ለመራመድ የኢትዮጵያው ጨዋታ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው።”
ቡድናቸው ውስጥ ስላሉት በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾች
”ብዙ አዳዲስ ተጫዋቾችና ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ አሉ ፤ ይህ በጣም ጥሩ ነው። እነሱን ማቀላቀላችንን መቀጠል አለብን። ምክንያቱም የዚህ ቡድን ተተኪና መፃኢ እድል እነሱ ናቸው። በቡድኑ ውስጥ ምቾት እንዲሰማቸው ማድረግ ወሳኝ ነው።”
ቡድኑ ስለጀመረው አዲስ አካሄድ
”አዎ እውነት ነው ፤ አዲስ ጅምር ነው። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከዚህ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተሰሩትን ሁሉንም ነገሮች መርሳት የለብንም። ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ተከናውነዋል። አሁን ያንን አጠናክረን መቀጠል አለብን። ወጣቶቹ እዚህ አሉ ፤ ዝግጁ ናቸው። ልምድ እንዲያገኙና እንዲጫወቱ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ዓርብ ዕለት ያደረግነውም ይኸው ነው ፤ ማክሰኞም ከፈጣሪ ጋር የምናደርገው ይሄው ነው። እስከ አፍሪካ ዋንጫው ድረስ ይሄንኑ እንቀጥላለን።”

